አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀገርን መገንባት በአንድ ትውልድ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን የሁላችንም የጋራና ቀጣይነት ያለው ሥራ ነው አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በተገኙበት “ከለውጥ ወደ ዘላቂ ሽግግር” በሚል መሪ ቃል “ኢትዮጵያ ታከናውናለች” የተሰኘ ብሔራዊ ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ በዚህ ጉባኤ ላይ መገኘቴ በየደረጃው የተጓዝንበትንና አሁን የደረስንበትን መንገድ መለስ ብዬ እንድቃኘው አድርጎኛል ብለዋል።
ሀገራችን በራሷ አቅም ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመገንባት፣ ያልተሞከሩ ግዙፍ ልማቶችን በማከናወን በየጊዜው ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረች ትገኛለች ነው ያሉት።
እነዚህ ሁሉ በአጋጣሚ የተገኙ ድሎች ሳይሆኑ በመደመር መንፈስ ላይ ተመስርተው መሆኑን ጠቅሰው፤ ዘላቂ ለውጥ የሚመጣው በጋራ በመቆም ነው በሚል ጽኑ እምነት የተወሰዱ ቆራጥ ውሳኔዎች የተገኙ ውጤቶች ናቸው ብለዋል፡፡ የጀመርናቸው ለውጦች በራሳቸው የመጨረሻ ግብ አይደሉም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይልቁንም ከእኛ በኋላ ለሚመጡት ተከታታይ ትውልዶች የምንጥለው ጠንካራ መሠረት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ሀገርን መገንባት በአንድ ትውልድ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን የሁላችንም የጋራና ቀጣይነት ያለው ሥራ ነው በማለት ገልጸው፤ በዚህ ጽኑ እምነት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይህንን መንፈስ ይዞ ወደፊት እንዲጓዝና የተቀበለውን ወረት አግዝፎ ይበልጥ ወደ ላቀ ከፍታ እንዲያመራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡