የሀገር ውስጥ ዜና

የአማራ እና የደቡብ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ከነገ ጀምሮ ለተከታታይ 5 ቀናት የሚቆይ የአመራሮች ስልጠና ሊሰጡ ነው

By Meseret Demissu

August 30, 2020

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 24 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ እና የደቡብ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ከነገ ጀምሮ ለተከታታይ 5 ቀናት የሚቆይ የአመራሮች ስልጠና ሊሰጡ መሆኑ ተገለጸ።

በሁለቱ ክልሎች የሚሰጠው ስልጠና ከነሐሴ 25 እስከ 30/2012 ዓ.ም ድረስ ለተከታታይ 5 ቀናት የሚቆይ  መሆኑ ተገልጿል።

የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ከነሐሴ 25  ጀምሮ ለተከታታይ 5 ቀናት በሚቆየው በዚህ ስልጠና የከፍተኛና የመካከለኛ አመራሮች  ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

ስልጠናው የመሪዎችንና የአባላትን አቅም ለመገንባት ለቀጣይ ተልዕኮዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ ከማዘጋጀት ባለፈ በዓላማ ደረጃም ሀገሪቱን ወደ ፊት ማሻገር የሚያስችል ፓርቲ በመገንባት ዴሞክራሲንና ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሆነም ተመላክቷል።

በስልጠናው 732 የክልል፣ የዞንና ወረዳ መሪዎች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

በስልጠናው የቆይታ ቀናት ከሰልጣኞች በሚጠበቁ ተግባራት ዙሪያ በፓርቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ መሰጠቱን አብመድ ዘግቧል።

በተመሳሳይ ዜና የደቡብ  ክልል ብልፅግና ፅ/ቤት ከነገ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የአመራር ስልጠና ሊሰጥ  መሆኑ ተገልጿል።

ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መገለጫ÷  ከ13 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አመራሮች ስልጠና እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ነገ በሚጀምረው የአሰልጣኞች ስልጠና 550 አመራሮች የሚሳተፉ ሲሆን÷ ቀሪዎቹ በሚቀጥሉት ግዜያቶች ስልጠና የሚያገኙና በክልሉ የሚገኙ አባላትና ደጋፊዎችም ስልጠናው  እንደሚሰጣቸው  ተናግረዋል  ።

የአቅም ግንባታ ስልጠናው በሁለት ክፍል የተዘገጀ ሰነድ ሲሆን ÷በዚህም ስልጠና ባለፉት ሁለት ዓመታት የተገኘውን አዎንታዊ ውጤት ለማስቀጠልና በአንፃሩ የተከሰቱ ለውጥ ቀልባሽ ተግባራትን ለመቅረፍ የራሱ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል  ተብሏል ።

በስልጠናውም በቂ ግንዛቤ በመፍጠር የሀገሪቱን ብልፅግና ለማረጋገጥና ጠንካራ አመራሮችን ከመፍጠርም ባለፈ  ወቅታዊ ሁኔታዎችን ተረድቶ የሚሰራ አመራር ለማዘጋጀት ይረዳልም  ብለዋል።

ከዚያም ባለፈ ስልጠናው በአመራሩ  ውስጥ የሚታዩ የአስተሳሰብ እና የተግባር ክፍተቶችን በመለየትና በማስተካከል የህዝብን ፍላጎት ተረድቶ ያሉ ችግሮችን ለይቶ ለመፍትሄ  የሚሰራ እንዲሆን ማስቻልም ጭምር መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም በክልሉ በርካታ አዳዲስ አመራሮች  በመኖራቸው በወቅታዊ የኮሮና ቫይረስ  እና መሰል ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ ከፖርቲው የብልፅግና ጉዞ ጋር በማያያዝ ለማስገንዘብ ታሳቢ መደረጉንም ተናግረዋል ።

በተለያዩ አካባቢዎች ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ የሚነሱ የመዋቅር ጥያቄዎችን አመራሩ ህግና መርህን ተከትሎ በብቃት እንዲመልስ ፓርቲው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ስለሆነም  ማንኛውም አይነት ጥያቄ ለሰዎች መጎዳትና ለንብረት መውደም ምክንያት መሆን የለበትም ነው ያሉት ፡፡

ሃላፊው አያይዘውም  በክልሉ የተፈጠሩ ችግሮችን ተከትሎም ከፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ጀምሮ  ከከፍተኛ  እስከ ዝቅተኛ አመራሮች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ባልደረባችን  ብርሃኑ በጋሻው ዘግቧል።