አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ መካሄዱ ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲያዊ አስተዳደርና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል አለ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ)፡፡
የኢጋድ ዋና ፀሀፊ ወርቅነህ ገበየሁ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት መካሄዱን በማስመልከት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ፓርቲያቸው ብልፅግና በምርጫው ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት በማሸነፋቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫው ሂደት ላሳየው ሙያዊ ብቃት ኢጋድ እውቅና ይሰጣል ያሉት ዋና ፀሀፊው፥ ኢትዮጵያውያን ያሳዩት ንቁ ተሳትፎ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡
ይህም ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲያዊ አስተዳደርና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
ምርጫው በስኬት መጠናቀቁ ኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነትን ለማጎልበት፣ ሁሉን አቀፍ ውይይትን ለማጠናከር እንዲሁም ሰላምንና ዘላቂ ልማትን ለማስቀጠል ለምታደርገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡
ኢጋድ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቀጣናዊ ትብብር እና ውህደት እንዲሁም በሰላምና መረጋጋት ዘርፍ ያለውን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡