አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በከምባታ ዞን ዱራሜ ከተማ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አስጀምረዋል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ530 ሚሊየን በላይ ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል።
በዚህም እስከ ሐምሌ 25 ቀን ድረስ ባሉት ቀናት በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች መርሐ ግብሩ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል።
መርሐ ግብሩ ሀገርን ከሚለውጡ ፕሮግራሞች መካከል እንደሆነ እና ይህም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍ የላቀ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
እንዲሁም ለምግብ፣ ለመድሀኒት፣ ለቁሳቁስ መስሪያነት እና ለሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተተከሉ መሆኑን ገልጸው፤ በተለያዩ ጊዜያት እየተተከሉ ያሉ ችግኞች የጽድቀት መጠን እየጨመረ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
የክልሉ ሕዝብ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ላይ በንቃት እየተሳተፈ እና በዚህም የከርሰ ምድር እና የገጸ ምድር የውሃ አካላት መጨመሩን አንስተው፤ የክልሉ ህዝብ በመርሐ ግብሩ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በክልሉ ከ530 ሚሊየን በላይ ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል።