አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በሀዋሳ ከተማ አስጀምረዋል ።
አቶ ደስታ ሌዳሞ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ÷ በአረንጓዴ ዐሻራ የለሙ አካባቢዎች ለብዙዎች የሃብት ምንጭ መሆን መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ የለሙ አካባቢዎችን ይበልጥ ጥበቃ በማድረግ የሃብት ምንጭ እንዲሆን መትጋት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ በንቃት ከመሳተፍ ባሻገር የተተከሉ ችግኞችን በተገቢ ሁኔታ እንዲንከባከብ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ መምህሩ ሞኬ በበኩላቸው ÷ በአረንጓዴ ዐሻራ የክልሉን የደን ሽፋን ማሳደግ፣ የአፈር መሸርሸርን መከላከልና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን አብራርተዋል፡፡
ለ2018 በጀት ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ326 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ነው ያመላከቱት፡፡
በዚህም ሀገር በቀል ዛፎች፣ የቡና ችግኞች፣ የፍራፍሬ፣ ለእንስሳት መኖ የሚውሉ እና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ላላቸው ችግኞች ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡
በብርሃኑ በጋሻው