የሀገር ውስጥ ዜና

ለቀጣናዊ ችግሮች ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ጠንካራ ተቋም ተገንብቷል – ጄ/ል ይመር መኮንን

By Melaku Gedif

June 25, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ የጦርነት ባህሪን በመረዳት ለአሁናዊ የቀጣናችን ችግሮች ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚችል ጠንካራ ተቋም ተገንብቷል አሉ የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ሃላፊ ጄነራል ይመር መኮንን።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመከላከያ ኮሌጅ ዓመታዊ የብሔራዊ ደህንነት ኮንፈረንስ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡

ጄ/ል ይመር በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ከምንጊዜውም በላይ እየተወሳሰበ የመጣው ዓለም አቀፋዊ የደህንነት ሁኔታ በርካታ ኢ ተገማች ችግሮችን እያስከተለ ነው፡፡

የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ጠንካራ ተቋማት እና ሀገር መገንባት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የአንድን ሀገር ደህንነት በተሟላ መንገድ ማረጋገጥ የሚቻለው ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሥጋቶችን ያገናዘበ የመፍትሔ አቅጣጫ ማፍለቅ ሲቻል በመሆኑ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ በየወቅቱ የሚያዘጋጃቸው ውይይቶች ለበላይ አካል ውሳኔ ሰጪነት ምቹ ናቸው ብለዋል።

እያንዣበበ ያለውን የጦርነት ደመና ለመግፈፍና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ውስጣዊ ችግሮችን መቅረፍና በውጭ ተጋላጭነቶች ላይ ማተኮር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ይህንን ለማስፈጸም መከላከያ ሠራዊቱ ሁሉን አቀፍ ዝግጅት አድርጓል ማለታቸውንም የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል።

የመከላከያ ዋር ኮሌጅ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ጥላሁን ደምሴ በበኩላቸው ፥ የቀጣናዊ ስጋት ለመፍታት በሳል ዲፕሎማሲና ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ እንቅስቃሴ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።