የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ የቀጣናው የኃይል እና የሎጂስቲክስ ማዕከል…

By Yonas Getnet

June 25, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ የሕዳሴ ግድብና የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የቀጣናው የኃይልና የሎጂስቲክስ ማዕከልነት እያረጋገጡ ነው አሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)።

6ኛው የኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በለንደን ከተማ ተካሂዷል።

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው አማካኝነት የውጭ ምንዛሪ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ለቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ይበልጥ የተረጋጋ፣ ተወዳዳሪና አስቀድሞ ሊተነበይ የሚችል ምቹ ምህዳር ፈጥራለች።

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያደረገች ያለውን ሂደት ያነሱት ሚኒስትሩ፥ መንግስት በተሰናሰለ መልኩ ተቋማዊ ግልጽነትን በማሻሻል ባለሀብቶች የሚያነሷቸውን ስጋቶች ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑንም አመልክተዋል።

በተለይም ለታዳሽ ኃይል ልማት በተሰጠ ልዩ ትኩረት ኃይል ማመንጨት የጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ የኃይል ማመንጫዎች የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ ኢትዮጵያን የቀጣናው የኃይል ማዕከል እያደረጓት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአቪዬሽን፣ ሎጂስቲክስ፣ ግንባታና ቱሪዝም ዘርፎች ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮችንና የሥራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዘርፍ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እንዲሁም በማዕድን ዘርፍ በተለይም የወርቅ ምርትን በማሳደግ ትልቅ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ነው ያሉት።

በአረንጓዴ ትራንስፖርት ዘርፍ 17 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች ሥራ መጀመራቸውንና በፈረንጆቹ 2030 ቁጥራቸውን ወደ 60 ለማድረስ መታቀዱን አብራርተዋል።

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ትንበያ መሠረት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዚህ ዓመት በ9 ነጥብ 2 በመቶ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ትንበያ 10 ነጥብ 2 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የብሪታንያ የንግድ ተቋማት በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች በመሳተፍ የዚህ የዕድገት ጉዞ አካል እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በብሪታኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብሩክ መኮንን በበኩላቸው፥ ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ለግሉ ዘርፍ ተዘግተው የቆዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች በፋይናንስ ተቋማት ሪፎርሞች ተደግፈው ክፍት መደረጋቸውን አንስተዋል፡፡

በፎረሙ ላይ አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማትና የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮችን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዮናስ ጌትነት