የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ መተመኛ ጥናት ቀረበ

By Yonas Getnet

June 26, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋን ሳይንሳዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመምራት የመተመኛ ጥናት ቀርቦ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ቅድስት ወ/ጊዮርጊስ እንዳሉት፤ ከተማ አስተዳደሩ የኑሮ ጫናን ለመቀነስና በየመኖሪያ ቤት ኪራይ ገበያው ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ሕገ ወጥና ዘፈቀዳዊ አሰራሮችን ለመግታት እየሰራ ነው።

በ2016 ዓ.ም በከተማዋ ሰፊ የአከራይና ተከራይ ውል ምዝገባ ማከናወኑን አስታውሰው፤ ይህም በቤት ልማትና አስተዳደር ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተና በዘፈቀደ የሚደረጉ ያልተገቡ አሰራሮችን ያስቀረ ትልቅ ስኬት ነበር ብለዋል።

በዛሬው ዕለት ደግሞ አዋጁ በሚሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት የውል ማደስ ሂደት ፍትሃዊ፣ ሳይንሳዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመምራት የተከናወነው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ መተመኛ ጥናት መቅረቡን ተናግረዋል።

ያለአግባብና በየጊዜው የሚጨምር የቤት ኪራይ ዋጋ የዜጎችን የመክፈል አቅም በማዳከም ለአጠቃላይ የዋጋ ንረት መባባስ አንድ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ጥናቱ በመዲናዋ ሁለንተናዊ ዕሴቶች ላይ የራሱ የሆነ እጅግ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳዎች እንዳሉት አብራርተዋል።

ጥናቱ አከራዩ ከንብረቱ ተገቢውንና የወቅቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ ያገናዘበ ፍትሃዊ ገቢ እንዲያገኝ የሚያረጋግጥ እንደሆነ እና በሌላ በኩል ደግሞ ተከራዩ ከገቢው ጋር የተመጣጠነ ኪራይ በመክፈል የተረጋጋ የኢኮኖሚ ህይወት እንዲመራ ያደርጋል ነው ያሉት።

በተጨማሪም ገበያውን ጤናማና ሊተነበይ የሚችል በማድረግ የከተማዋን የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንደሚያረጋጋ ገልጸው፤ የቤት ኪራይ ዋጋ መረጋጋት ቤተሰቦች በተደጋጋሚ ቤት ከመቀየር ስጋት ይታደጋቸዋል ብለዋል።

ግልጽና ሕጋዊ አሰራርን በመዘርጋት በአከራይና ተከራይ መካከል የነበረውን ያለመተማመን መንፈስ እና የደላሎችና የሕገ ወጥ ደላሎችን ጣልቃ ገብነት እንደሚያስቀርም አመልክተዋል።

ይህ ዛሬ የቀረበው የዋጋ ትመና ጥናት በዘፈቀደ የተሰራ ሳይሆን የከተማዋን ነዋሪ የመክፈል አቅም ማገናዘቡን ገልጸዋል።

ጥናቱን የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ እና የተለያዩ የዩኒቨርሲቲ መምህራን እንዳከናወኑ ጠቅሰው፤ በ2019 በጀት ዓመት እንደሚተገበር ጠቁመዋል።

በመድረኩ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላት፣ የመኖሪያ ቤት አከራዮች እና ተከራዮች ተሳትፈዋል።

በመሳፍንት እያዩ