የሀገር ውስጥ ዜና

የአማራ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄደ

By Mikias Ayele

June 26, 2026

አዲሰ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2018 (ኤፍ.ኤም.ሲ) የአማራ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ÷ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማኅበራዊ ትስስርን የበለጠ በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያሰፋ ይገኛል ብለዋል።

“በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ ” በሚል መሪ ሀሳብ በመላ ኢትዮጵያ እየተከናወነ የሚገኘው የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በአማራ ክልልም 15 ሚሊየን ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ደም መለገስ፣ ለአቅመ ደካሞች ማዕድ ማጋራት፣ ችግኝ መትከልና የቤት ግንባታ ፕሮጀክት ርክክብ የማድረግ ተግባራት አከናውነዋል።

በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 16 አገልግሎቶች የተካተቱ ሲሆን 9 ነጥብ 8 ሚሊየን በጎ ፈቃደኞች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በክልሉ 100 የበጎ ፈቃድ ሞዴል ቀበሌዎችን ለመፍጠርም እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በክልሉ ከ18 ሺህ በላይ አቅመ ደካሞችንና ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ቤቶች ግንባታ ይከናወናል የተባለ ሲሆን፤ በአጠቃላይ 20 ቢሊየን ብር የሚገመት አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል።

ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ አመራርና ነዋሪዎች ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ልዩ ትኩረት በመስጠት የሚፈለገውን ግብ ለማሳካት ርብርብ እንዲደረጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በደሳለኝ ቢራራ