የሀገር ውስጥ ዜና

ዲጂታል ኢኮኖሚ በኢትዮጵያ ….

By Abiy Getahun

June 26, 2026

በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዓለማችን በከፍተኛ የቴክኖሎጂ ምጥቀት ውስጥ ትገኛለች። የዲጂታል ተጠቃሚነት የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ዕጣ ፈንታ የሚወስን ዋነኛ ሞተር ሆኗል።

ኢትዮጵያም ይህንን ማከናወን የህልውና ጉዳይ መሆኑ ገብቷታል፡፡ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለኢትዮጵያ ቅንጦት ሳይሆን የሀገሪቱን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ የመኖርና ያለመኖር ያህል አስፈላጊ ነው።

የኢትዮጵያ በዚህ ረገድ በከፍተኛ የሪፎርም እና የሽግግር ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። መንግሥት ቀደም ሲል የነበረውን የ2025 ስትራቴጂ አሳክቶ፣ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን አዲሱ ብሔራዊ ፍኖተ-ካርታው አድርጎ መሥራት ጀምሯል። የዚህ ስትራቴጂ ዋና ግብ እስከ 2030 የዲጂታል ኢኮኖሚው ለሀገሪቱ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ወደ 12 በመቶ ማሳደግ ነው።

ዲጂታል ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር ለማረጋገጥ ምሰሶ ነው፡፡ የስራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋት፣ የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማቀላጠፍ እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ፣ የገበያ ተደራሽነት እና የንግድ ውድድርን ለማሳደግ ፍቱን ነው፡፡

የዲጂታል ኢኮኖሚ መስፋፋት ሀገሪቱን ወደ ዕውቀት-መር ኢኮኖሚ እንድትሸጋገር በማድረግ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እና የሥራ ዕድል ፈጠራን ያረጋግጣል፡፡ ወጣቶች በቴክኖሎጂ የታገዙ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን በስታርትአፖች በመሥራትና ወደ ንግድ በመቀየር ራሳቸውንና ሌሎችን የሚቀጥሩበት ዕድል እየተፈጠረ ነው። በሶፍትዌር ልማት፣ በመረጃ ትንተና፣ በዲጂታል ማርኬቲንግ እና በሳይበር ደኅንነት ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዘመናዊ እና አዳዲስ የሥራ ዕድሎች እየተፈጠሩ ይገኛሉ።

የመንግሥት አገልግሎቶችን በማቀላጠፍ እና መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንጻር ዲጂታል ኢትዮጵያ ወሳኝ ነው፡፡ ባህላዊው የመንግሥት አሠራር በቢሮክራሲ የተወሳሰበ፣ የወረቀት ክምር የበዛበት እና ለሙስና የተጋለጠ ነው። አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ጉዞ ተጀምሯል፤ ለዚህ ደግሞ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተጠቃሽ ነው፡፡

እንደ ታክስ አሰባሰብ፣ የንግድ ፈቃድ ዕድሳት እና የሲቪል ምዝገባ ያሉ አገልግሎቶች በኦንላይን ሲሆኑ ግልጽነትና ተጠያቂነት ሰፍኖ የተገልጋዩ እንግልት ይቀንሳል፤ ለሙስና የሚያጋልጡ ቀዳዳዎችም ይዘጋሉ።

የመንግሥት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ የፋይዳ መታወቂያ እና የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን ተችሏል፡፡ እስካሁን ከ41 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ውስጥ የተመዘገቡ ሲሆን፣ ይህ መታወቂያ ለባንክ፣ ለጤና እና ለሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች ዋነኛ መታወቂያ እየሆነ ነው። ከ130 በላይ የመንግሥት አገልግሎቶች ለታክስ ክፍያ፣ ለሲቪል ምዝገባና ለንግድ ፈቃድ እድሳትና አዲስ ለማውጣት በኦንላይን እንዲከናወኑ ተደርገዋል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ እና የፊንቴክ እድገትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው፡፡ በኢትዮ ቴሌኮም የቴሌብር መተግበሪያ እና በባንኮች የሞባይል ባንኪንግ አማካኝነት የካሽ አልባ ግብይት ሥርዓት በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ነው። በአዲሱ የብሔራዊ ዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ (2026-2030) የሕግ ማሻሻያዎችን በማድረግ የውጭ ሀገር ዜጎች እና የዲያስፖራ ማህበረሰብ በሀገር ውስጥ የፊንቴክ እና የቴክኖሎጂ ስታርትአፖች ላይ በቀጥታ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ተፈቅዷል።

ዲጂታል ኢትዮጵያ የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ ፍቱን ነው፡፡ ባህላዊው የባንክ ሥርዓት በቅርንጫፎች ውስንነት ምክንያት አብዛኛውን የገጠርና የከተማ ዝቅተኛ ማኅበረሰብ ተደራሽ ማድረግ አልቻለም ነበር። የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ግን ይህንን ሽሯል።

እንደ ቴሌብር እና የባንኮች የሞባይል ገንዘብ መተግበሪያዎች ምስጋና ይግባውና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ያለ ባንክ ቅርንጫፍ በስልካቸው መቆጠብ፣ መበደር እና መክፈል ችለዋል። ይህ አሰራር ባንክ አልባውን ማኅበረሰብ መድረስ ችሏል፡፡

የካሽ-አልባ ግብይት መስፋፋት የገንዘብ ኖት ማተሚያ ወጪን ከመቀነሱም በላይ የንግድ እንቅስቃሴን እያፋጠነ ይገኛል።

የዲጂታል ኢኮኖሚ የቦታና የርቀት ገደቦችን እያስቀረ ነው። የኢ-ኮሜርስ መድረኮች አምራቾችንና ሸማቾችን በቀጥታ ያገናኛሉ። ይህም አሰራር የገበያ ተደራሽነት እና የንግድ ውድድርን እያሳደገው ነው፡፡

አርሶ አደሩ ምርቱን ያለደላላ በዲጂታል ገበያ አማካኝነት ቀጥታ ለገዢዎች በማቅረብ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ እያስቻለው ነው፡፡ የሀገር ውስጥ የዕደ-ጥበብ፣ የቡና እና የሌሎች ምርቶች አምራቾች የዲጂታል መድረኮችን በመጠቀም ምርቶቻቸውን ለዓለም አቀፍ ገበያ በቀላሉ ማስተዋወቅና መሸጥ ይችላሉ።

በአጠቃላይ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለኢትዮጵያ አማራጭ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው። ሀገሪቱ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የዲጂታል ኢኮኖሚው ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት 12 በመቶ እንዲያበረክት ግብ አስቀምጣ እየሰራች ነው፡፡

ይህንን ለማሳካት የመሠረተ-ልማት ግንባታን የማጠናከር፣ የኢንተርኔት ታሪፍን የማመጣጠን እና የኅብረተሰቡን የዲጂታል ክህሎት የማሳደግ ሥራ እየሰራች ትገኛለች፡፡ የዲጂታል ሽግግሩ ሲፋጠን ሁለንተናዊ የኢትዮጵያ ብልጽግናም እውን ይሆናል።

ኑ፤ ሀገር እንሥራ!