ስፓርት

የዓለም ዋንጫው ተጠባቂ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች…

By Hailemaryam Tegegn

June 26, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ዋንጫ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይደረጋሉ፡፡

በምድብ ዘጠኝ ያደረጓቸውን ሁለቱንም ጨዋታዎች በማሸነፍ አስቀድመው 32ቱን የተቀላቀሉት ፈረንሳይ እና ኖርዌይ ምድቡን በበላይነት ለማጠናቀቅ ይፋለማሉ፡፡

በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ ለሀገራቸው በተመሳሳይ አራት ግቦችን ያስቆጠሩት ኪሊያን ምባፔ እና ኧርሊንግ ሀላንድ ምሽት 4 ሰዓት በሚደረገው ጨዋታ ይጠበቃሉ፡፡

በዚሁ ምድብ በተመሳሳይ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ኢራቅን የምትገጥመው አፍሪካዊቷ ሀገር ሴኔጋል የምሽቱን ጨዋታ የምታሸንፍ ከሆነ ምርጥ ሦስተኛ በመሆን 32ቱን ለመቀላቀል የተሻለ እድል አላት፡፡

እስካሁን አላፊው ብሔራዊ ቡድን ባልታወቀበት ምድብ ስምንት ስፔን ከዩራጓይ እንዲሁም ኬፕ ቨርዴ ከሳዑዲ አረቢያ ሌሊት 9 ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡

አራት ነጥቦችን በመሰብሰብ ምድብ ሰባትን እየመራች የምትገኘው ግብጽ ነገ ማለዳ 12 ሰዓት ላይ ከኢራን ጋር የምትጫወት ሲሆን፥ ቤልጂየም ከኒውዚላንድ በተመሳሳይ ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡

እስካሁን ሜክሲኮ፣ አሜሪካ፣ካናዳ፣ ጀርመን፣ አርጄንቲና፣ ፈረንሳይ፣ ኖርዌይ፣ ኮሎምቢያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ቦሲኒያ ሄርዞጎቪና፣ ብራዚል፣ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኤኳዶር፣ ኮትዲቯር፣ ኔዘርላንድስ፣ ጃፓን፣ ስዊድን፣ አውስትራሊያ ከምድባቸው ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡