ገበታ ለትውልድ…

By Abiy Getahun

June 26, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ገበታ ለትውልድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት ይፋ የሆነ፣ የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ በማሳደግ ትልቅ ታሪካዊ ምዕራፍ የከፈተ ግዙፍ ብሔራዊ የልማት ፕሮጀክት ነው።

ይህ መርሐ ግብር ቀደም ሲል በአዲስ አበባ የተተገበረውን ገበታ ለሸገር እና በክልሎች የተከናወነውን ገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችን ስኬት ተንተርሶ፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ እምቅ የተፈጥሮ፣ የባህልና የታሪክ ጸጋዎችን ለዓለም ለማስተዋወቅና ለመጪው ትውልድ የሚተርፍ ቅርስ ለማስቀመጥ የተወጠነ ነው።

ፕሮጀክቱ በዋናነት የመንግሥት፣ የሕዝብ፣ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ እና የባለሀብቶች ጥምር የፋይናንስና የዕውቀት አስተዋጽኦ የተደመረበት ነው።

በዚህ መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ በልዩ ልዩ ክልሎች የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች ተለይተው ግንባታቸው ተከናውኗል፤ እየተከናወኑም ይገኛሉ፡፡

በደንዲ የእሳተ-ገሞራ ሐይቅ ላይ የተገነባው የሀሮ ደንዲ ሎጅ፣ የተፈጥሮ ሥነ-ምህዳሩን ሳይበክል ዘመናዊ ሥነ-ሕንጻን ከተፈጥሮ ውበት ጋር በማቀናጀት ግዙፍ የኢኮ-ቱሪዝም መዳረሻ ሆኗል።

በሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ውብ የሐይቅ ተፈጥሮንና የወሎን ሕዝብ ጥልቅ ባህላዊ እሴት ለዓለም የሚያስተዋውቅ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሪዞርት ተገንብቷል።

የአርባ ምንጭ የኮንፈረንስ ሪዞርት አርባ ምንጭ ያላትን ሰፊ የቱሪዝም ጸጋ (የአባያና ጫሞ ሐይቆች፣ የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ) መሠረት በማድረግ የተገነባ ሲሆን ለኹነቶችና ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ምቹ ያደርገዋል።

የጅግጅጋ ፕሮጀክት በሶማሌ ክልል የሚገኘውን የባህልና የተፈጥሮ መስህብ ይበልጥ በማልማት የቱሪስት ፍሰቱን ለማሳደግ የተከናወነ ነው።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሰው ሰራሽ ሐይቅንና የአካባቢውን ድንቅ ውበት ወደ ቱሪስት መስህብነት ለመቀየርም በሌላ በኩል እየተሰራ ነው፡፡

እጅግ አስደናቂ የተራሮች አቀማመጥ የሚገኝበትን የገራልታ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና መልከዓ-ምድርን በመሠረተ-ልማት በማስተሳሰር ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ እቅድም ተተግብሯል፡፡

የቡና መገኛ የሆኑትንና የተፈጥሮ ጥብቅ ደን የሚገኝባቸውን ጅማ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን በኢኮ-ሎጅ ለማልማት እየተሠራ ነው።

ፕሮጀክቶቹ የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆን የሥራ ዕድል መፍጠር እየቻሉ ሲሆን፤ የውጭ ምንዛሪ እና የቱሪዝም እድገትን በማረጋገጥ ለሀገር በጎ ገጽታ ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል፡፡

ግንባታዎቹ ከተጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ለአካባቢው ወጣቶችና ማኅበረሰብ ሰፊ የሥራ ዕድል የፈጠሩ ሲሆን፤ የሀገር ውስጥ ምርትንና ቁሳቁስን በመጠቀም የአካባቢውን የንግድ እንቅስቃሴ አነቃቅተዋል።

ቀደም ሲል በመሠረተ-ልማት እጦት ተደብቀው የቆዩ የተፈጥሮ መስህቦች ተገልጠው የሀገር ውስጥ የቱሪዝም ልምምድ እየተነቃቃ ሲሆን፤ የውጭ ሀገር የቱሪስቶች ፍሰትንና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝትም እያሳደጉት ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለች፣ የምትመኘውን በጥራትና በፍጥነት ማልማት የምትችል ሀገር መሆኗን ፕሮጀክቶቹ ለዓለም ማኅበረሰብ በተግባር ያሳዩ ህያው ምስክሮች ናቸው።