የሀገር ውስጥ ዜና

ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታችው የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ኢትዮጵያን ለመገንባት መትጋት አለባቸው

By Abiy Getahun

June 27, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታችሁ ያገኛችሁትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ኢትዮጵያን ለመገንባት መትጋት አለባችሁ አሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አለምፀሐይ ጳውሎስ።

ጅማ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ መርሐ ግብር ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 973 ተማሪዎች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር እንዲሁም የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አለምፀሐይ ጳውሎስ፤ ዛሬ የተመረቃችሁ ተማሪዎች የሀገራችን ውድ ሀብት ናችሁ ብለዋል።

ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው ኢትዮጵያን ለመገንባት እና ለማበልጸግ እንዲሁም ለእድገቷ የመፍትሔ አካል መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ ገና ያልተነኩ የልማት አቅሞች እንዳሉ ገልጸው፤ አንድነታችንን በማጠናከር ልማት ላይ መረባረብ አለብን ሲሉ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል አባፊጣ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በፈተና ሳትበገሩ ተግዳሮቶችን አልፋችሁ እዚህ በመድረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በርካታ ማኅበረሰብ አቀፍ ሥራዎችን እንደሚሠራ ጠቅሰው፤ ይህን ማስቀጠል የሁሉም የዩኒቨርሲቲው አካላት ኃላፊነት መሆኑን አክለዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎችን ብቃት ማጠናከር እና ምርምሮችን ማካሄድን ጨምሮ ዘርፈ-ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ራስ-ገዝ ተቋም ለመሆን ሂደቱን የሚያሟሉ ሥራዎችን በትጋት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።