አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ወራቤ ዩኒቨርስቲ ለ7ኛ ጊዜ በቅድመ እና በድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር በተለያዩ የትምህርትና የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 900 ተማሪዎች አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴዔታ ክንደያ ገ/ሕይወት (ፕ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሀገር የምትፈልገው የሞራል ልዕልና እና የሀገር ፍቅር ስሜት ያለው ተመራቂን ነው ብለዋል።
መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በትህምርት ሂደቱ መሠረት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የተሠራው ሥራ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
የዲጂታል ትግበራዎችን ዕውን በማድረግ በተለይ የተማሪዎች ምዘናን በበይነ መረብ መስጠት መቻሉ ኩረጃን ማስቀረት ችሏል ነው ያሉት።
ሀገር የምትፈልገው የሞራል ልዕልና እና የሀገር ፍቅር ስሜት ያለው ተመራቂ ነው ያሉት ክንደያ ገ/ሕይወት (ፕ/ር)፤ ከመቀጠር ዕሳቤ ተላቃችሁ በሥራ ፈጠራ፣ በታማኝነት እና በቅንነት ሀገራችሁን ልታገለግሉ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።
የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ቶውፊቅ ጀማል (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዛሬው ተመራቂ ተማሪዎች ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር በጊቢ ቆየታችሁ ያካበታችሁትን ዕውቀት ለሀገር በሚበጅ መልኩ ልትጠቀሙበት ይገባል ብለዋል።
ወደ ማኅበረሰቡ ስትቀላቀሉ ማንነታችሁን በሚገልፅና የዩኒቨርሲቲያችሁን አበርክቶ መሠረት ባደረገ መልኩ ሚናችሁን መወጣት አለባችሁ ሲሉ አስረድተዋል።
በወንድሙ አዱኛ