የሀገር ውስጥ ዜና

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 2 ሚሊየን 21 ሺህ ሔክታር በዘር ለመሸፈን…

By Yonas Getnet

June 28, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዘንድሮው የምርት ዘመን 2 ሚሊየን 21 ሺህ ሔክታር መሬት በዘር ለመሸፈን አስፈላጊው የዝግጅት ሥራ እየተጠናቀቀ ነው አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ባበክር ኸሊፋ እንዳሉት÷በክልሉ ባለፈው ዓመት ከለማው 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ሔክታር ዘንድሮ 400 ሺህ በመጨመር 2 ሚሊየን 21 ሺህ ሔክታር ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል።

ዕቅዱን በስኬት ለማጠናቀቅም ከባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ መግባባት በመፍጠርና የአደረጃጀት ሥራዎችን በመከወን እስከ ወረዳ ድረስ ግልጽ የሥራ ክፍፍል መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሒደት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሔክታር በላይ መሬት የጽዳት ሥራ መከናወኑን እና ከ630 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት ደግሞ በትራክተር ታርሶ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥ ከ500 ሺህ ሔክታር በላይ የሚሆነው ማሳ በዘር መሸፈኑን ጠቁመው÷ ቀሪውን በዘር የመሸፈን ተግባር በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ከግብዓት አቅርቦት ጋር በተያያዘ 131 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ 110 ሺህ ኩንታል ወደ ክልሉ የገባ ሲሆን÷ እስካሁን 80 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን አመልክተዋል።

የአርሶ አደሩን ፍላጎት መሰረት በማድረግ 4 ሺህ 500 ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር መሰራጨቱን ነው ሃላፊው የገለጹት፡፡ በአካባቢው በስፋት የሚመረቱት የማሽላ ዝርያዎች ጨምሮ ሩዝና ስንዴን የመዝራት እንቅስቃሴ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በወንዝ ዳርቻ የሚገኙና ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች የጎርፍ መከላከያ ግድቦችን በመስራት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

በዮናስ ጌትነት