አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የነዋሪዎች ጥያቄ እና መሰረታዊ ፍላጎት በተጨባጭ እየተመለሰ ነው አሉ፡፡
የእንጦጦ-ቀበና የወንዝና የወንዝ ዳርቻ ልማት እንዲሁም የቀበና ግድብ ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ አዲስ አበባ ለሕዝባችን ቅድሚያ የሚሰጣቸውንና ከተማዋ የሚመጥናትን ታላላቅ የልማት ሥራዎች በላቀ ብቃትና ትጋት እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።
ዛሬ ለከተማችን ድምቀት፣ ተጨማሪ ጌጥ እና የውበት ፀዳል ያላበሰውን የወንዝ ዳርቻ እና የግድብ ልማት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በተሰጠን የስራ መመሪያ መሰረት በጥራትና በፍጥነት አጠናቀን ለሕዝብ አቅርበናል ነው ያሉት።
ፕሮጀክቱ አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርጧ የቱሪስት መዳረሻ ብቻ ሳትሆን የውበት ማማ የሚያደርጋት ድንቅ ሥራ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 87 ነጥብ 6 ሔክታር መሬት እንደሚሸፍን ጠቁመው ÷ 10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በውስጡም የጋራ አገልግሎት መስጫዎችን እና የሕዝብ መገልገያዎችን አሟልቶ መያዙን ነው የገለጹት፡፡
ፕሮጀክቱ በታለመለት የጊዜ እና የጥራት ደረጃ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ከንቲባ አዳነች ምስጋና አቅርበዋል፡፡