አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከተፈጥሮጋር ተስማምተን መኖር እና መንከባከብ ካልቻልን የተፈጥሮ ቅጣት ከባድ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክትን በዛሬው ዕለት መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት ÷ ፕሮጀክቱ የግንባታ ስኬት ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባ ከተማ የአየር ንብረት ለውጥን የምትቋቋምና ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነች ከተማ የሚያደርግ ነው፡፡
ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ ለመኖር በውሃ፣ አፈር እና አየር ንብረት ላይ መስራት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ፕሮጅክቱ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የሚገባ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ መቆሸሽ፣ መጠልሸት፣ ማነስ እና ሌላ ሀገር ሄዶ መቅናት አይገባንም ነው ያሉት፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጀመር ከአንድም ሶስት ባለሙያዎች እትችሉም ብለውናል ፤ ሆኖም የለም እንችላለን በማለት ሰርተን እንደምንችል አስመስክረናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
በመሐል ጠፍተን ሊሆን ይችላል፤ ግን ጥንታዊያን ነን ብንደመር እና ብንተጋገዝ ውብ ሀገር ተሰጥቶናል የሚል መልዕክት በመናገር ብቻ ሳይሆን በመስራት ለባሕር ማዶ ተችዎች አሳይተናል ነው ያሉት፡፡
ማሕበረሰቡ የሚከናወኑ ሥራዎችን በተገለጠ ማንነት እንዲመለከት የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ለቀጣይ ድሎች በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡
በአቤል ነዋይ