የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ያደረጉት ህዝቦቿ ናቸው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By sosina alemayehu

June 29, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ናት፤ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ያደረጉት ህዝቦቿ ናቸው አሉ።

ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፥ ያስቀመጥናቸውን የምርጫ መንትያ ግቦች ያሳካው ህዝባችን ነው ብለዋል።

ምርጫው በከተማዋ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ እና ነፃ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ ላደረጉ ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበው፤ ሀገርን ማፅናት፣ ሰላምን ዘላቂ ማድረግ እና ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥ የኢትዮጵያ የመቻል ማሳያዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ከቴክኖሎጂ መስተጓጎል ጋር ተያይዞ ከፍጥነት ጋር በተያያዘ መጓተት ቢያጋጥምም፤ ነዋሪዎች ሳይሰላቹ ከማለዳ ጀምሮ እስከ ሌሊት በፅናት በመሰለፍ ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ፣ ልማት እንዲቀጥልና ሰላም እንዲሰፍን አድርገዋል ብለዋል።

ህዝቡ ብልፅግና ፓርቲን የመረጠው ምንም ችግር የለም በሚል ሳይሆን፤ ያልተመለሱ ጥያቄዎች በሂደት እንደሚመለሱ፣ ያልተጠናቀቁ ስራዎች እንደሚያልቁና የጎደለው እንደሚሞላ በማመን መሆኑን አስገንዝበዋል።

በዚህም የህዝብን አደራ በታማኝነት፣ በመሰጠት፣ በትጋትና በቁርጠኝነት እንደሚወጡና አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ አስተዳደራቸው በቀን 24 ሰዓት በሳምንት 7 ቀናት (24/7) በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።