አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እየተጠናከረ የመጣው የኢትዮጵያና ሶማሊያ ትብብር በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ላይ የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ድንበር ብቻ ሳይሆን የጋራ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነት እና ወግ የሚጋሩ እንዲሁም ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ እና ማህበራዊ ግንኙነት ያላቸው የቅርብ ጎረቤቶች ናቸው፡፡
አልሻባብን ጨምሮ በሀገሪቱ የተፈለፈሉ የአሸባሪ ኃይሎችን ኢትዮጵያና የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በትብብር የቀጣናውን የሽብር ስጋት ለመቀልበስ ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት ስኬት አስመዝግበዋል።
የኢትዮጵያና የሶማሊያ የረጅም ጊዜ ግንኙነት በተለያየ ጊዜ ፈተና ቢገጥመውም፣ ሁሉንም ውጣ ውረዶች አልፎ ዛሬ ላይ አዲስ ምዕራፍ ጀምሯል።
ሀገራቱ ከድንበር ግንኙነት ባለፈ ለቀጣናዊ መረጋጋት፣ ትስስር እና ዕድገት እውን መሆን ግንኙነታቸውን አድሰው በትብብር መንፈስ እየሰሩ ይገኛሉ። የዚህ አዲስ ምዕራፍ ማሳያ ደግሞ በከፍተኛ አመራር ደረጃ የሚደረጉት ተከታታይ ውይይቶች ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼኽ መሃሙድ በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በተደጋጋሚ ፍሬያማ ምክክር አድርገዋል።
ጥቅምት 2 ቀን 2018 ዓ.ም መሪዎቹ ባደረጉት ውይይት በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ትብብራቸውን ለማጠናከር የሚያስችል ቆይታ አድርገዋል።
እንዲሁም ከ38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን በነበራቸው ቆይታ ዳግም በቁልፍ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የታደሰው የሀገራቱ ግንኙነት ወጥነት ያለው ተከታታይ ሥራ እንደሚፈልግ አስገንዝበዋል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የትብብር ማዕቀፍ ፣ የህዝቦችን የጋራ ዕጣ ፈንታ እና ቀጣናዊ ልማት ማዕከል በማድረግ ጠንካራ ጉዞ ጀምሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት ከሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼኽ መሐሙድ ጋር በሁለትዮሽ ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በኢኮኖሚያዊ ትሥሥር፣ በሰላምና ደኅንነት እንዲሁም በቀጣናዊ መረጋጋት ላይ መክረናል ብለዋል።
ሀገራቱ የሚጋሩት ከድንበር ያለፈ ሕዝቦቻቸውንና መፃዒ መዳረሻቸውን ጭምር መሆኑንም አመላክተዋል።
በሚኪያስ አየለ