አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዘላቂና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይልን በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂ እየተዘጋጀ ነው አለ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት መርሐ ግብር ምዕራፍ ሦስት ትግበራን የተመለከተ አውደጥናት አካሂዷል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የኤሌክትሪክ ኃይል ለዕድገትና ለማንኛውም ዓይነት የልማት እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው።
በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ ታዳሽ፣ ዘላቂና አስተማማኝ የኃይል ተደራሽነት የኢትዮጵያን ብልፅግና እና ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ያሏትን የኃይል አማራጭ ምንጮች ለመጠቀም የኃይል ማመንጨት አቅምን ማሳደግ እንዲሁም የኃይል አማራጮችን የማሻሻል ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ለብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት መርሐ ግብር ትግበራ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲያድግ ለማድረግ የኢነርጂ ፖሊሲ ክለሳ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በመርሐ ግብሩ የሦስተኛው ምዕራፍ ትግበራም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ንጹሕ ኢነርጂን ማስፋፋት፣ ለምርታማነት ተግባራት ቅድሚያ መስጠትና የዘርፉን ዲጂታላይዜሽን አሠራር ማጠናከር ላይ የሚያተኩር መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህ ምዕራፍ ትግበራ ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው÷ በሁለቱ ምዕራፎች ያጋጠሙ ክፍተቶችን ለመፍታት በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
ቀጣናዊ የኃይል ትስስርን በማጠናከር ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ኃይል በማቅረብ የአህጉሪቱን ሁለንተናዊና የተቀናጀ ልማት በማሳለጥ ቀጣናዊና አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ለማጠናከር እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በበኩላቸው÷ የኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ሥራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ትግበራ እስከ 2035 ድረስ ባሉት ዓመታት የኤሌክትሪክ ኃይልን በመላ አገሪቱ ለማዳረስ መታቀዱን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) ናቸው።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሪፊኬሽንና ኢነርጂ መረጃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ዳቢ ÷ የብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን የሚመራ ስትራቴጂ ለማዘጋጀት ከአንድ ዓመት በላይ ጥናት ሲካሄድ ቆይቷል ብለዋል።