አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የበጎ ፍቃድ ሥራ ከልማት ውጤቶች በተጨማሪ ማሕበራዊ ትስስርን፣ መረዳዳትንና ወንድማማችነትን ያጠናክራል አሉ በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ነመራ ቡሊ።
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዘርፎች የሚከናወነው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በጅማ ዞን ሶኮሩ ወረዳ ተጀምሯል፡፡
አቶ ነመራ ቡሊ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የኢትዮጵያን እድገት ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ለማድረግ መንግሥት ከሚከውናቸው ሥራዎች ጎን ለጎን እየተተገበረ ያለው የዜግነት አገልግሎት ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው።
አገልግሎቱ ከልማት ውጤቶች በተጨማሪ ማህበራዊ ትስስርን፣ መረዳዳትን እና ወንድማማችነትን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው ÷በዞኑ የክረምት በጎ ፍቃድ ሥራ ባለፈው ዓመት ወጣቶችንና ባለሃብቶችን በማሳተፍ ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተወጣጡ ወጣቶችን በማሳተፍ በ72 የሥራ ዘርፎች ላይ እንደሚከናወን አስረድተዋል።
ማሕበረሰቡ፣ባለሃብቶች፣ ምሁራንና ወጣቶች ባላቸው ጉልበት፣ ገንዘብና እውቀት ከሕዝባቸው ጎን በመቆም በተጀመረው በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በተስፋሁን ከበደ