የሀገር ውስጥ ዜና

የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት በዓለም ከፍተኛ ተጓዦች ከተመረጡ 5 ቅርሶች ውስጥ ተካተቱ

By Hailemaryam Tegegn

June 30, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት በዓለማችን ከፍተኛ ተጓዦች ከተመረጡ የዩኔስኮ ምርጥ አምስት ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ ተካትተዋል፡፡

የዓለም ሀገራትን በመጎብኘት “ዩኤን ግራንድማስተር” የተባለውን ታዋቂ የክብር ማዕረግ ያገኙ ቁንጮ ተጓዦች ለጉብኝት የሚመክሯቸውን ምርጥ የጉዞ መዳረሻዎች ይፋ አድርገዋል።

በታዋቂው የዜና አውታር ‘ዩሮኒውስ’ በተደረገ ጥናት መሰረት እነዚህ አንጋፋ ተጓዦች ካስቀመጧቸው ተወዳጅ የዩኔስኮ የዓለም ቅርሶች መካከል የላሊበላ ውቅርአብያተ ክርስቲያናት በምርጥ 5 ምርጫዎች ውስጥ መካተት ችሏል።

ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰጠ ምስክርነት ኢትዮጵያ አስደናቂ ታሪክና አስገራሚ ጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት መሆኗን በድጋሚ ያረጋገጠ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

ተጓዦቹ እንደ አንኮር ዋት እና ታላቁ የቻይና ግንብ ካሉ ታዋቂ ቅርሶች ጎን ለጎን ስለ ላሊበላ ድንቅ የጥበብ ጥልቀትና መንፈሳዊ ግርማ ምስክርነታቸውን መስጠታቸው ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ሊታይ የሚገባው ቀዳሚ የጉዞ መዳረሻ መሆኑን አመላክቷል።

ይህንን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ይበልጥ ለማጎልበት የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናትን ከተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች በመጠበቅና በመንከባከብ በዘላቂ የቅርስ ልማትና ጥበቃ መርሆዎች መሰረት ለትውልድ ለማስተላለፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለጎብኚዎች ምቹና ደኅንነቱ የተጠበቀ በማድረግ የቱሪዝም ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማሳደግ የቅርስ ጥበቃ ሥራዎችን ከዘመናዊ መሠረተ ልማት ጋር በማቀናጀት እየተሰራ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡