አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለቱሪዝም ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት መነሾ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ የማስረከብ ራዕያችን ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አዲሱ የኢኮኖሚ ሞተር” በሚል በቱሪዝም ዙሪያ ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ግዙፍ አቅም በመጠቀም የዜጎችን ሕይወት መቀየርና የሀገርን ገጽታ መገንባት ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ በግብርና ላይ ብቻ የተንተራሰ ኢኮኖሚ መገንባት ታስብ እንደነበር አንስተው፥ ይህ ደግሞ በአጭር ጊዜ የበለጸገች ሀገርን እውን ማድረግ አላስቻለም ነው ያሉት፡፡
በዚህም ሀገሪቱ በብዘሀ ዘርፍ ኢኮኖሚ መመራት እንዳለባት በማሰብ ከተለዩ አምስት ዋና ዋና ዘርፎች መካከል አንዱ ቱሪዝም መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በዓለም ላይ በየዓመቱ 12 ነጥብ 6 ትሪሊየን ዶላር በቱሪዝም ዙሪያ እንደሚንቀሳቀስ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህንን በመገንዘብ ቱሪዝም ከአምስቱ የኢኮኖሚ አምዶች ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ከዚህ ሀብት ኢትዮጵያ ብሎም አፍሪካ ምን ያህሉን ይቋደሳሉ የሚለው ቁልፍ ጥያቄ እንደሆነ ገልጸው፥ ከዘርፉ ከፍተኛ ገቢ በማግኘት ኢኮኖሚውን ለመደገፍ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ቱሪዝም ለአንድ ዓላማ ብቻ የሚውል ባለመሆኑ የሚመጡት ጎብኚዎች የሀገር ውስጥ ምርትን እንዲሸምቱ፣ ለእውቀት ሽግግር እንዲሁም ኢንቨስትመንት መሳብን ጨምሮ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አስረድተዋል፡፡
በዓለም ላይ በየአመቱ ለ370 ሚሊየን ሰዎች በቱሪዝም ዘርፍ የሥራ እድል እንደሚፈጠር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለዘርፉ ትኩረት የተሰጠበት ሌላኛው ምክንያት ለሥራ እድል ፈጠራ ያለው ሚና መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ቱሪዝም ለውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትና ለኢንዱስትሪ ዘርፉ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፥ አነስተኛ የንግድ አንቀሳቃሾችን ተጠቃሚ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ በማሳደግና የጎብኚዎች ቁጥር አንዲጨምር በመስራት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም አሟጥጣ እንደምትጠቀም አስረድተዋል፡፡
በአቤል ነዋይ