አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሚሳተፉ የዱባይ ባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች አሉ።
አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከዱባይ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሐመድ አሊ ሉታህ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት 36 አባላት ያሉት የንግድ ልዑክ መርተው በአዲስ አበባ በቅርቡ ጉብኝት ያደረጉት መሐመድ አሊ ሉታህ፤ ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው የማክሮኢኮኖሚ ማሻሻያ በተጨባጭ ለመመልከት መቻላቸውን ተናግረዋል።
ይህ ሰፊና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ በዱባይ ባለሀብቶች ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑንም አክለዋል።
ከማሻሻያው በመነሳት በምክር ቤቱ ስር የሚገኙ ትላልቅ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቅሰዋል።
በተለይም በቅርቡ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት በሆነው የኢትዮጵያ የፋይናንስና የባንክ ዘርፍ ውስጥ በይፋ ለመግባት ከፍተኛ ዝግጅት መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዱባይ ንግድ ምክር ቤት በአዲስ አበባ ለበርካታ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ጋር ያደረገው የቢዝነስ ለቢዝነስ ግንኙነት ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ፋይናንስ፣ ግብርና፣ ታዳሽ ኃይልና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ለሚገቡ የዱባይ ባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍና ማበረታቻ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።
ውይይቱ ከዚህ ቀደም ሁለቱ ኃላፊዎች የዱባይ ባለሀብቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ካደረጉት ቅድመ ዝግጅት እና በቅርቡ በግንቦት ወር በአዲስ አበባ በተሳካ ሁኔታ ከተካሄደው የኢትዮ-ዱባይ ቢዝነስ ትስስር መድረክ ቀጥሎ የተደረገ መሆኑ ተገልጿል።