አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2018 በጀት ዓመት ብቻ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ የውጭ ሀገራት ዜጎች የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻዎች ጎብኝተዋል አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አዲሱ የኢኮኖሚ ሞተር” በሚል በቱሪዝም ዙሪያ ባደረጉት ልዩ ቃለ ምልልስ ላይ እንዳሉት ፥ ኢትዮጵያ በተከተለችው የብዝሃ ዘርፍ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በሁሉም ዘርፎች አስደማሚ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው።
በ2018 በጀት ዓመት 10 ነጥብ 2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚጠበቅ ጠቅሰው ÷ ይህ የኢኮኖሚ ዕድገትም ከአፍሪካ አህጉር በኢትዮጵያ ብቻ ሊመዘገብ የሚችል ነው ብለዋል።
በቱሪዝም ዘርፍ ታይቶ የማይታወቅ የቱሪስት ፍሰትና የገቢ ዕድገት ተመዝግቧል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በበጀት ዓመቱ ብቻ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውን አስረድተዋል፡፡
አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከ100 ሺህ በላይ፤ ከ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ ከ300 ሺህ በላይ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል፡፡
በውጭ ቱሪስት ፍሰትና ተያያዥ እንቅስቃሴዎች ከ5 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማግኘት መቻሉን ነው የገለጹት፡፡
ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና ኮንፈረንሶችን በማስተናገድ ረገድ ትልቅ ስኬት መመዝገቡን ጠቁመው ÷ በዓመቱ ኢትዮጵያ 204 ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን ማስተናገዷን አስገንዝበዋል፡፡
በእነዚህ ኮንፈረንሶች ብቻ 166 ሺህ የውጭ እንግዶች ተሳትፈዋል ፤ ይህ የሰዎች፣ የገንዘብና የቱሪስት ፍሰት መጨመርም የኢትዮጵያን ዓመታዊ ገቢ ወደ 1 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር ለማሳደግ ትልቅ አቅም እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡
በሶስና አለማየሁ