አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከማንኛውም ሉዓላዊ ሀገር መሠረታዊ ምሰሶዎች መካከል የጸጥታ ተቋማት ከፍተኛውን ስፍራ ይይዛሉ።
የመከላከያ ኃይል፣ የመረጃ ተቋማት፣ ፖሊስ እና ሌሎች የደህንነት መዋቅሮች የሀገርን ድንበር፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት፣ የዜጎችን ደህንነት እና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ያስጠብቃሉ።
ሆኖም ግን የጸጥታ ተቋማት ተለዋዋጭ የፖለቲካ፣ የቴክኖሎጂ፣ የክልላዊና የዓለም አቀፍ የደህንነት ሁኔታዎችን ተከትለው ራሳቸውን ማሻሻል ይገባቸዋል።
የጸጥታ ተቋማት ሪፎርም ማለት የመከላከያ፣ የፖሊስ፣ የመረጃ እና የፍትሕ ተቋማት ውጤታማ፣ ሕጋዊ፣ ተጠያቂ እና ለሕዝብ አገልጋይ እንዲሆኑ የሚደረግ የተቋማዊ ለውጥ ስራ ነው።
ሪፎርም የተቋማትን መዋቅር፣ አመራር፣ የሰው ኃይል፣ የሕግ ማዕቀፍ፣ ቴክኖሎጂ እና የተጠያቂነት ሥርዓት ማሻሻልን ያካትታል።
ኢትዮጵያም ከዚሁ በመነሳት በጸጥታ ተቋማቷ ላይ ባለፉት ዓመታት በርካታ ሪፎርሞችን አድርጋለች፡፡
ለአብነት ያህል በኢትዮጵያ መከላከያ ዘርፍ የተደረገው ሪፎርም ከሰራዊት አደረጃጀት አንጻር የእዝ አወቃቀርን ለማዘመን የኮማንድ መዋቅሮች ተሻሽለዋል፣ የመሬት፣ የአየር እና የልዩ ኃይሎች ቅንጅት እንዲጠናከር ተደርጓል።
እንዲሁም የዲጂታል ኮማንድና የመረጃ ስርዓቶች ተጠናክረዋል፡፡
የአየር ኃይልን ለማጠናከር አዳዲስ መሣሪያዎች፣ ቴክኖሎጂዎችና አውሮፕላኖች ባለቤት መሆን ተችሏል።
የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ለተለያየ ዓላማ በሰፊው ጥቅም ላይ መወላቸው የሪፎርሙ ውጤት ነው።
በተጨማሪም የባህር ኃይልን መልሶ ለማቋቋም በርካታ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን አዲስ የባህር ኃይል እንደገና በመገንባት የሰው ኃይል ስልጠናና ድርጅታዊ መዋቅር ማጠናከር እና ተቋሙን ማዘመን የሚጠቀሱ የለውጥ ስራዎች ናቸው፡፡
በሌላ በኩልፖሊስ የውስጥ ሰላምን ለማስጠበቅ ወሳኝና የመጀመሪያው ተቋም ነው። የፖሊስ ሪፎርም በሕግ የበላይነት፣ በሙያዊነት፣ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ እና በማህበረሰብ ተሳትፎ ላይ መመስረት አለበት።
በተጨማሪም የወንጀል ምርመራን በዘመናዊ ፎረንሲክ ቴክኖሎጂ፣ በዲጂታል መረጃ ትንተና እና በመረጃ ቋት ማደራጀትና ማጠናከር ያስፈልጋል።
በዚህም በፌዴራል ፖሊስ ከፎረንሲክ ጋር ተያይዞ የተከናወኑ የለውጥ ስራዎች የወንጀል ምርመራን ዘመናዊ፣ ተዓማኒ እና በሳይንሳዊ ማስረጃ የተደገፈ እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርገዋል።
የቴክኖሎጂ ልማት፣ የሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ የላቦራቶሪ ማሻሻያ እና የምርመራ ሥርዓት ማዘመን ወደፊትም የፍትሕ ሥርዓቱን የበለጠ ለማጠናከር ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ሰፊ ድንበሮች ሕገወጥ የሰው ዝውውር፣ የመሣሪያ ዝውውር፣ የሽብር ቡድኖች እንቅስቃሴ እና የድንበር ግጭቶችን ለመከላከል ዘመናዊ የድንበር ቁጥጥር የሚያስፈልግ በመሆኑ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል።
ከሳይበር ደህንነት ጋር በተያያዘም በዲጂታል ዘመን የሀገር ሉዓላዊነት በመሬት ብቻ የሚወሰን ባለመሆኑ የባንክ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የመንግሥት መረጃ ሥርዓቶች እና ወሳኝ መሠረተ ልማቶች ከሳይበር ጥቃት መጠበቅ የብሔራዊ ደህንነት ዋና አካል ሆኗል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የጸጥታ ተቋማት ሪፎርም ከሀገር ሉዓላዊነት አንጻር ሲታይ ብሔራዊ ደህንነትን፣ የህግ የበላይነትን፣ የሕዝብ እምነትን እና የመንግሥት ተቋማዊ ብቃትን ለማጠናከር ወሳኝ ሂደት ነው።
በአመለወርቅ ደምሰው