አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለውን እምቅ የማዕድን ሃብት በዘመናዊ መንገድ ለማልማት በቅንጅት መስራት ይገባል አለ የክልሉ ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ፡፡
የክልሉ ግብርና እና ማዕድን ዘርፍ አጋር አካላትን ትብብር ለማጠናከር ያለመ ውይይት በግልገል በለስ ከተማ ተካሂዷል፡፡
የክልሉ ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቱጃኔ አደም በወቅቱ እንዳሉት÷ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ያልተነካና በሚገባ መልማት የሚችል እምቅ የማዕድ ሃብት አለ፡፡
ይህንን ሃብት ዘመኑን በዋጀ መንገድ ለማልማትና ጥቅም ላይ ለማዋል መንግሥት በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከልና ፈር ለማስያዝ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
በክልሉ ግብርና ቢሮ የእንስሳት ዘርፍ ም/ኃላፊ ብርሃኑ ኢትቻ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የግብርና ዘርፉን ውጤታማነት ለማጠናከር የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ማስገኘታቸውን አንስተዋል።
የተቀናጀ የግብርና አሰራር ሥርዓትን በመዘርጋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ሚና ሊጠናከር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በክልሉ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የግብርና ዘርፉን ይበልጥ ለማዘመን በተደራጀ መልኩ እየተሰራ መሆኑንና በየደረጃው የተጠናከረ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መለሰ ኪዊ÷ የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ግብ ለማሳካት የተቀናጀ የግብርና ሥርዓትን መዘርጋትና አርሶ አደሩ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በዞኑ ምርታማነትን ለማሳደግና ዘላቂ ብልጽግናን እውን ለማድረግ መደበኛ የግብርና ሥራዎችን ማጠናከር ላይ ትኩረት በማድረግ የግብርና ልማት ኢኒሼቲቮችን ለማስፋት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በመላኩ ገድፍ