የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሊዮን በረራ ጀመረ

By abel neway

July 01, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፈረንይ ሊዮን ከተማ የመንገደኞች በረራ አገልግሎት ማስጀመሩን ይፋ አድርጓል።

ይህም ለአየር መንገዱ በፈረንሳይ 3ኛ፣ በአውሮፓ 23ኛ እንዲሁም የዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን ቁጥር 146 የሚያደርሰው መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በወቅቱ እንዳሉት፤ የበረራ አገልግሎቱ መጀመር አየር መንገዱ አፍሪካን ከዓለም ጋር የማገናኘት ጉዞው ተጨማሪ ስኬት ነው።

ወደ ሊዮን የጀመረው በረራ ለዓለም አቀፍ ተጓዦች ተጨማሪ ዕድል የሚፈጥር ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡

መንገደኞችን ከማመላለስ ባሻገር የሀገራት ሁለንተናዊ ትስስሮች እንዲጠናከሩ አቅም መፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

አየር መንገዱ የዘመኑን ቴክኖሎጂ የታጠቁ ግዙፍ አውሮፕላኖችን በማስፋፋት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በቀጣይም የመዳረሻ ቁጥሩን ለመጨመር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በአቪየሽን ኢንዱስትሪ ዓመታትን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸውም አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲ ላሜክ በበኩላቸው የኢኮኖሚ ማዕከል ወደሆነችው ሊዮን የተጀመረው በረራ የሀገራቱን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን ለማሳደግ እየሰራ ሲሆን፤ በቢሾፍቱ አየር መንገድ ግንባታ ሒደት የፈረንሳይ ተቋማት በጥናትና በልዩ ልዩ ዘርፎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡

በሔኖክ ለሜ