የሀገር ውስጥ ዜና

የትውልዱ የቱሪዝም ዘርፍ አለኝታ ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት …

By Abiy Getahun

July 01, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እልፍ በሆኑ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች የተሞላች ነች፤ ነገር ግን ቀደም ሲል ለዘርፉ በተሰጠው አነስተኛ ግምትና አስተዳደራዊ ችግሮች ሳቢያ እነዚህ ሀብቶች ለዐይን የማይሞሉ፣ ጎብኚዎችን የማይስቡ፣ ከገቢም አንጻር ይህ ነው የማይባል አስተዋፅኦ ሳይኖራቸው ዘመናት ተቆጥረዋል።

ከሀገራዊ ለውጥ በኋላ ቱሪዝም እንደ ሀገሪቷ የብልጽግና ምሰሶነት ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ችሏል።

በዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ተጠንስሰው ለፍሬ በቅተዋል።

እነዚህ ፕሮጀክቶች የሀገርን እምቅ ውበት ከመግለጥ አንጻር ከፍተኛ እመርታን እያሳዩ ሁለንተናዊ እድገትንም ለማረጋገጥ በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ወሳኝ ርምጃ ሆነው ውጤታቸው መታየት ጀምሯል።

ከገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው በስሙ የሚጠራ ከተማ የተሰየመለት በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ በተሁለደሬ ወረዳ የሚገኘው የሎጎ ሐይቅ አንዱ ነው፡፡

ይህ ሐይቅ ከአዲስ አበባ በ430 ኪሎ ሜትር፤ ከደቡብ ወሎ ዞን መቀመጫ ደሴ ከተማ ደግሞ በ30 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከሐይቅ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

ከ23 እስከ 88 ሜትር ጥልቀት ያለው ሐይቁ ከባህር ወለል በላይ 1 ሺህ 950 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ የሚሸፍነው የመሬት አካል ደግሞ 35 ስኩዌር ኪሎ ሜትር በላይ ነው።

ይህ ሐይቅ የተንሰራፋበት መልክዓ ምድር በሰንሰለታማ ተራሮች የተከበበ፣ ለዕይታ ማራኪ፣ የበርካታ ጎብኚዎችን ቀልብ መሳብ የሚችል ሃብቱ ያለተነካ ድንቅ የመስህብ ስፍራ ነው፡፡

ሐይቅ ከተማ ኢትዮጵያውያን የሚታወቁበት የአብሮነት እሴት በተጨባጭ የሚታይበት ስፍራ እንደሆነ በርካቶች ይስማሙበታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቦታውን እንዲህ ሲሉ ገልጸውት ነበር፤ “ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ገራገርና ቅን የሆነውን የወሎ ሕዝብ ውብ ባህልና እሴት ለማስተዋወቅ ያስችላል፤ ክርስትና እና እስልምና ተዋደው እና ተከባብረው የሚኖሩበት ድንቅ አከባቢ፤ የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ደግሞ የስፍራው ታላቅ ሃብት ነው”፡፡

በዚህ ከተማ የሚገኘው ትልቅ ውበት ነው ታድያ፤ ከትኩረት ማጣት አንጻር ከተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ብሎም ከዓለም ዕይታ ተሸሽጎ የቆየው።

በገበታ ለትውልድ ውጥን ፕሮጀክቶች ስር በመታቀፍ ቀን ከሌት ስራው በጥራትና በፍጥነት ተከናውኖ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጥር ወር 2018 ዓ.ም ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።

በሐይቁ ላይ የተገነባው ሪዞርት በመደመር እሳቤ መንግሥትንና የግሉን ዘርፍ በአንድነት በማሳተፍ የተገኘውን ውጤት ጽኑ መሰረት እንዲኖረው አስችሏል፡፡

በ13 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ምግብ ቤቶችን፣ የመዋኛ ገንዳዎችን፣ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገዶችን እና የሄሊኮፕተር ማረፊያን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት አገልግሎቶችን በአንድነት ይዟል፡፡

ልዩ ልዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ስፍራዎች፣ ለዕይታ የሚማርኩ አረንጓዴ አካባቢዎችን አቅፎ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ሀገራት ጎብኚዎች የማይረሳ ትዝታን የሚፈጥር ውብ ቦታ ነው፡፡

የቱሪዝም ልማትን ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ ከዘላቂ እና ከአካታች ሁለንተናዊ እድገት ጋር በማቀናጀት፣ ሪዞርቱ የወሎ ሕዝብ ያለውን ታላቅ ባህላዊና ተፈጥሯዊ እሴት ለተቀረው ዓለም ማኅበረሰብ ማስተዋወቅ የሚቻልበት ሰፊ ገበታ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ ለማህበረሰቡ የስራ ዕድልን ከመፍጠር ባሻገር የአካባቢውን ቱሪዝም፣ የትራንስፖርት እንዲሁም የግብርና ዘርፎች የሚያነቃቃ በተጨማሪም ለአምራቾችና ስራ ፈጣሪዎች አዲስ የገበያ ትስስርን በመፍጠር ለኢኮኖሚ እድገትና ብልጽግና አለኝታ ሆኖ ያገለግላል።

በመልካም ፍቃዱ