አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሁሉም ዘርፎች የታየው የተቀናጀ የሰዎች፣ የገንዘብና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተደምሮ የኢትዮጵያን ዓመታዊ አጠቃላይ ገቢ ለማሳደግ ትልቅ አቅም ይኖረዋል አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ቱሪዝም አዲሱ የኢኮኖሚ ሞተር በሚል ርዕስ ባደረጉት ቆይታ፥ ኢትዮጵያ በተከተለችው የብዝሃ ዘርፍ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ነው፡፡
በግብርና፣ ቴክኖሎጂ፣ ፋይናንስ፣ ኢንዱስትሪ እና ማዕድን ዘርፎች በከፍተኛ ፍጥነት ምላሽ እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል።
በግብርናው ዘርፍ በስንዴ፣ በቡና፣ በአበባና በፍራፍሬ ልማት ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸው በሌማት ትሩፋትም በዶሮና ወተት ምርት ከፍተኛ መነቃቃት መፈጠሩን አስረድተዋል።
በቴክኖሎጂው ዘርፍ የ5 ሚሊየን ኮደሮች ስራ እና የዲጂታል መታወቂያ ትግበራ የዲጂታል ኢኮኖሚውን እያሳደገው መሆኑንም አመልክተዋል።
በፋይናንስ ዘርፍ በተለይም ቴሌብር 55 ሚሊየን ተጠቃሚዎችን በመያዝ በሀገሪቱ የጂዲፒ ድርሻ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ኢንዱስትሪው የተሻለ ወጪ ንግድ የሚገኝበትና የሶላር ምርቶችን ጭምር ኤክስፖርት የሚደረግበት መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
በተጨማሪም ቀደም ሲል ከ30 እስከ 40 ሚሊየን ዶላር የማይበልጥ ገቢ ይገኝበት የነበረው የማዕድን ዘርፍ አሁን ላይ ቢሊየን ዶላሮችን እያስገኘ ነው ብለዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ቱሪስት እንቅስቃሴ እጅግ አስገራሚ መነቃቃት እያሳየ እንደሚገኝ ጠቁመው ዘንድሮ ከ50 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ መዳረሻዎችን መጎብኘታቸውን አመልክተዋል፡፡
ይህም ከአምናው በ1 ነጥብ 8 ሚሊየን፣ ከ2016 ዓ.ም ደግሞ በ9 ነጥብ 4 ሚሊየን ብልጫ አለው ብለዋል፡፡
በሁሉም ዘርፎች የታየው የተቀናጀ የሰዎች፣ የገንዘብና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተደምሮ የኢትዮጵያን ዓመታዊ አጠቃላይ ገቢ ለማሳደግ ትልቅ አቅም እንደሚሆን አስገንዝበዋል።
በሶስና አለማየሁ