የሀገር ውስጥ ዜና

ኮሚሽኑ በምክክር ጉባዔ ወቅት ሙያዊ ማብራሪያ ከሚያቀርቡ ልሒቃን ጋር እየተወያየ ነው

By Hailemaryam Tegegn

July 02, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በምክክር ጉባዔ ወቅት ሙያዊ ማብራሪያ ከሚያቀርቡ ልሒቃን ጋር እየተወያየ ነው፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ በሀገራዊ ምክክር ሒደት ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታትና ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል ምሕዳር ተፈጥሯል፡፡

ላለፉት አራት ዓመታት ሰፊ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመው፥ በዚህም በተለያዩ ምዕራፎች ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ ማካሄድ የሚያስችል አሳታፊና አካታች የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊ ልየታ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል ።

4 ሺህ ተሳታፊዎች ያሉት የምክክር ጉባዔው በ8 ቡድኖች የተዋቀረ ሲሆን÷ ኢትዮጵያን የሚመስልና ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተወከለበት እንዲሆን በጥንቃቄ መደራጀቱን አስረድተዋል፡፡

ልሒቃኑ በምክክሩ ሒደት የጋራ መረዳት እንዲፈጠር፣ የውስብስብ ጉዳዮችን ታሪካዊ አመጣጥና የታዩ ክስተቶችን በጥናት አስደግፈው በማመላከት ወደ መፍትሄ ማድረስ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ተወያዮች በአንድ ሳምንት ውስጥ ወደ አዲስ አበባ እንደሚገቡና ቢያንስ ለ4 ሳምንታት የሚቆይ ውይይት እንደሚያደርጉም ዋና ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡

በምንተስኖት ሙሉጌታ