የሀገር ውስጥ ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የገጠር ኮሪደር ልማት አካል የሆነውን ሀማሳ ሞዴል መንደር መረቁ

By Yonas Getnet

July 02, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የገጠር ኮሪደር ልማት አካል የሆነውን ዘመናዊው የሀማሳ ሞዴል መንደር በዛሬው ዕለት በይፋ መርቀዋል። ‎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ በ79 ነጥብ 4 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውና የገጠር ኮሪደር ልማት አካል የሆነው ዘመናዊው የሀማሳ ሞዴል መንደር ዛሬ በይፋ ተመርቋል ብለዋል።

‎መንደሩ የአርሶ አደሩን ኑሮና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያግዙ ዘመናዊ የመታጠቢያ ክፍሎች፣ የእንስሳት ማደሪያ፣ የአትክልት ስፍራ፣ የባዮ ጋዝ እና የንብ ቀፎዎች የተሟሉለት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ለነዋሪዎች ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚያረጋግጥ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አጽንኦት የሰጡት፡፡

መንደሩ የገጠሩን ማሕበረሰብ ክብር፣ ምቾት እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ የሪፎርሙ ሕያው ፍሬ እንደሆነም አውስተዋል፡፡