የሀገር ውስጥ ዜና

ለሀገር የወል ጥቅም ቅድሚያ መስጠት አለብን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Hailemaryam Tegegn

July 02, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የግል ጥቅምን ብቻ ከማሰብ ይልቅ ለሀገር የወል ጥቅም ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በጋሞ ዞን የሚገኘውን ‘ዮ ሆልዲንግ’ የድንጋይ ከሰል ፋብሪካ የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ 5 ቢሊየን ዶላር ገደማ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን የድንጋይ ከሰል እስከ 300 ሚሊየን ዶላር ወጪ በማድረግ ከውጭ ይገባ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ካለፈው ዓመት መጨረሻ ወዲህ ብቻ አራት የድንጋይ ከሰል ማምረቻ ፋብሪካዎች ተመርቀው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ፋብሪካዎች አሁን ያለውን የሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪዎች ፍላጎት መመለስ የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡

በቀጣይ ወደ ሥራ የሚገቡ ተጨማሪ ፋብሪካዎች መኖራቸውን ጠቁመው፥ በዚህም የድንጋይ ከሰል ምርቶችን ለውጭ ገበያ የማቅረብ እድላችን ሰፊ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የድንጋይ ከሰል ምርቶቹ የጥራት ችግር እንደሌለባቸው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በተወሰነ ደረጃ የሚስተዋሉ የልምድ ችግሮች እየተሻሻለ እንደሚሄዱ አመልክተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በደቡብ አፍሪካ የድንጋይ ከሰል እያመረቱ ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡ የነበሩ አካላት የኢትዮጵያን ምርቶች የማራከስ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ይስተዋላል ነው ያሉት፡፡

እነዚህ አካላት የውጭ ምንዛሪ ከሀገር በማውጣትና ሸቀጦችን ወደ ሀገር በማስገባት የራሳቸውን መክበር ብቻ የሚያስቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የግል ጥቅምን ብቻ ማሰብ ትክክል አለመሆኑን ገልጸው፥ ለሀገር የወል ጥቅም ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በሀገር ውስጥ ፋብሪካ ሲሰራ የሚፈጥረው የሥራ እድል ተጨማሪ ጥቅም መሆኑን ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ÷ ከውጭ በገፍ ይገቡ የነበሩ የተለያዩ ምርቶች በሀገር ውስጥ እየተመረቱ ነው ብለዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ