የሀገር ውስጥ ዜና

ሪዞርቱ ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ መድረኮች ማዕከል የማድረግ ርዕያችንን ያጠናክራል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Hailemaryam Tegegn

July 04, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ መድረኮች ማዕከል የማድረግ ርዕያችንን ያጠናክራል አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በገበታ ለትውልድ መርሐ ግብር የተገነባውን የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት በዛሬው ዕለት መርቀው ሥራ አስጀምረዋል፡፡

ዘመናዊ ሪዞርቱ በሐይቅ ላይ የተገነባ ልዩ ተንሳፋፊ ሬስቶራንት እና ከ1 ሺህ 300 በላይ ሰዎችን የሚያስተናግድ የስብሰባ አዳራሽን ያካተተ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ዛሬ ያስመረቅነው የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት የ‘ገበታ ለትውልድ’ መርሐ ግብራችን ያፈራው ሌላኛው ታላቅ ስኬት ነው ብለዋል።

ሪዞርቱ ከመዲናችን ባሻገር የኮንፈረንስ ቱሪዝምን በማስፋፋት ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ መድረኮች ማዕከል የማድረግ ርዕያችንን ያጠናክራል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል፡፡ ‎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው መላው የሀገራችን ሕዝብ፣ ዳያስፖራውና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ይህንን አዲስ የሀገራችንን ዕንቁ ስፍራ በመጎብኘትና በመጠቀም የኢትዮጵያን አዲስ የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ምዕራፍ በጋራ እንድንቋደስ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።