የሀገር ውስጥ ዜና

የበይነመረብ መገናኛ ብዙሃን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም…

By Mikias Ayele

July 04, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የበይነመረብ መገናኛ ብዙሃን ለኢትዮጵያ ሰላምና ብሔራዊ ጥቅም መከበር አዎንታዊ ሚና ሊጫወቱ ይገባል አለ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን፡፡

ባለሥልጣኑ “የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም” በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው መድረክ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሐይማኖት ዘለቀ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የበይነመረብ መገናኛ ብዙሃን ተመዝግበውና ዕውቅና አግኝተው እንዲንቀሳቀሱ ተደርጓል፡፡

በአሁኑ ወቅት 73 የበይነመረብ መገናኛ ብዙሃን በሕጋዊ መንገድ መመዝገባቸውን ገልጸው፥ እነዚህ መገናኛ ብዙሃን የመረጃ ተደራሽነትና የሐሳብ ብዝሃነትን በማረጋገጥ ለኢትዮጵያ ሰላምና ብሔራዊ ጥቅም መከበር አዎንታዊ ሚና እየተወጡ ነው ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከዚህ በተቃራኒው ቴክኖሎጂውን ለአሉታዊ ዓላማ በመጠቀም የሕዝብና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉና የሀገርን ሰላም የሚያናጉ አካላት መኖራቸውንም ነው የገለጹት፡፡

እነዚህን ጎጂ ልምምዶች አስወግዶ ቴክኖሎጂውን በእውቀትና በኃላፊነት ለመምራት አሁን ላይ የሁሉም አካላት ርብርብና ቅንጅት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የበይነመረብ መገናኛ ብዙኃን የሀገርን ሉዓላዊነት፣ የሕዝብ ደኅንነትና የኢኮኖሚ ዕድገትን ከማስከበር አንጻር ሚዛናዊና ሙያዊ ሥነ ምግባርን የተከተለ ሚና እንዲጫወቱ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን በመከላከልና ረገድ የመገናኛ ብዙሃንን አቅም ለመገንባት እየሠራ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡

በአንዱዓለም ተስፋዬ