አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለመላው አፍሪካ ትልቅ ምሳሌ የሚሆን የብልጽግና ጉዞ ጀምራለች አሉ።
በገበታ ለትውልድ መርሐ ግብር የተገነባው የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት በዛሬው ዕለት ተመርቆ በይፋ ሥራ ጀምሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ በሐምሌና በነሐሴ ወራት የሚከሰተውን የክረምት ቁር ለመሸሽ ምቹ የሆነችው አርባምንጭ ጎብኝዎችን በሁለት እጆቿ ተቀብላ ለማስተናገድ ዝግጁ ሆናለች ብለዋል።
ከተማዋ በሪዞርቶቿና በተፈጥሮ ውበቶቿ ብቻ ሳይሆን በባህላዊ ምግቦቿ እንግዶችን ለመቀበል መዘጋጀቷን ተናግረዋል።
ሰዎች ወደ ከተማዋ የሚመጡት ለመዝናናት ብቻ እንዳልሆነ ገልጸው ፥ በዚሁ አጋጣሚ እኛ ተጨማሪ የሀብት ልማት እንዲፈጠር ማድረግ ይገባናል ነው ያሉት።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸው እያስመዘገበችው ያለውን አህጉራዊ አርአያነት ተመልክተው ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ለመኖር ማሰብ የሚጀምሩበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ማድረግ ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ ታሪካዊ ተግባር እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ፊት እንዳትራመድና ወደ ኋላ እንድትጎተት የሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች የሚፈጥሯቸው ፈተናዎችና ችግሮች ቢኖሩም፤ ልማት፣ ሰላምና ብልጽግናን ስለምናስብ እያሸነፍን ጉዟችን እንቀጥላለን ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በ10 ነጥብ 2 በመቶ በሆነ ከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ የምትገኝ ብቸኛ ሀገር መሆኗን ገልጸው፥ ይህ ስኬት ለመላው ሕዝብ ኩራት በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ኢትዮጵያ ልጆቿን የምትሰበስብ፣ የአንድነትና የሰላም ምሳሌ ሆና እንደምትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
ይህ የአህጉሪቱ ምሳሌ የሆነው ዕድገት በተግባር የሚታይባቸውን እንደ አርባምንጭ፣ ጅማ፣ ሶዶ፣ ሀዋሳ፣ ነቀምቴ፣ ባሕርዳር፣ ድሬዳዋና ጅግጅጋ ያሉ በርካታ ከተሞች በምስክርነት ጠቅሰዋል።
በሶስና አለማየሁ