የሀገር ውስጥ ዜና

አዎንታዊ ትርክት ለሀገራዊ አንድነት ….

By Melaku Gedif

July 04, 2026

ሀገር የምትገነባው ወደ ኋላ በመመልከት ሳይሆን ወደ ፊት በመጓዝ ነው።

የጋራ ትርክት የሕዝቡን ስነ-ልቦና ከታሪክ ክርክርና ከፖለቲካ ንትርክ አውጥቶ ወደ ጋራ ራዕይ እንዲያዞር ያደርጋል።

ኢትዮጵያ ከ80 በላይ የሚሆኑ ብሔረሰቦች፣ የተለያዩ ባህሎች፣ ቋንቋዎችና እምነቶች በጋራ የሚኖሩባት የታሪክና የብዝሃነት ሀገር ናት።

ይሁን እንጂ ሀገሪቱ ያጋጠሟት አብዛኞቹ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች መነሻቸው ካለፈው ታሪክ፣ ከማንነት እና ከሀገር ግንባታ ሂደት ጋር በተያያዙ የትረካ ልዩነቶች መሆኑ ግልጽ ነው።

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት አካታችና ሚዛናዊ የሆነ የጋራ ሀገራዊ ትርክት መገንባት ለኢትዮጵያ ህልውና፣ አንድነትና ዘላቂ ሰላም ወሳኝና አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆኗል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ምህዳር ውስጥ በዋናነት ሁለት ጽንፍ የረገጡ የትርክት መስመሮች ይስተዋላሉ፡፡

አንደኛው የአንድነት ትርክት ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ የሀገሪቱን ታሪካዊ አንድነት እና ጥንታዊነት ብቻ በማጉላት፣ የብሔረሰቦችን ልዩ ማንነት እና የታሪክ ቁርሾዎችን የመዘንጋት አዝማሚያ ያሳያል።

ሁለተኛው የልዩነት ትርክት ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ በልዩነቶችና ባለፉት የታሪክ በደሎች ላይ ብቻ በማተኮር፣ አብሮ የመኖሩን እውነታ እና የጋራ እሴቶችን ወደ ጎን የመግፋት አዝማሚያ አለው።

እነዚህ እርስ በርስ የሚጋጩ ሁለቱ ትርክቶች በዜጎች መካከል መጠራጠርን፣ የሲቪክ ስብራትን እና የፖለቲካ አለመረጋጋትን ሲፈጥሩ ቆይተዋል። ስለዚህ እነዚህን ሁለት ጽንፎች አስታርቆ የሚጓዝ የጋራ ትርክት መገንባት የኢትዮጵያ ዋነኛ የቤት ሥራዋ ነው።

የጋራ ትርክት የኢትዮጵያን ብዝሃነት እንደ ስጋት ሳይሆን እንደ ትልቅ ጸጋ እና ውበት ይወስዳል። የብሔረሰቦችን ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ እውቅና በመስጠት፣ በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ ሁሉንም የሚያስተሳስር ኢትዮጵያዊ የጋራ ማንነትን ይገነባል። ይህ በብዝሃነት ውስጥ ያለ አንድነትን በተግባር ያረጋግጣል።

ካለፉት የታሪክ ቁርሾዎች ወጥቶ አዎንታዊ በሆኑ የጋራ ታሪኮች ለምሳሌ እንደ የዓድዋ ጦርነት የኢትዮጵያውያን ትመትና የጋራ ድል፣ የሕዳሴ ግድብ ርብርብ፣ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶች፣ የእርስ በርስ መጋባትና አብሮ መኖር ወዘተ… ላይ በማተኮር በሕዝቦች መካከል ያለውን የጥርጣሬ ግድግዳ ያፈርሳል።

መተማመን ሲሰፍን ደግሞ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድና በውይይት የመፈታት ዕድላቸው ከፍተኛ ይሆናል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የጀመረችው የሀገራዊ ምክክር ዋና ግብ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን መፍጠር ነው።

ጠንካራ የጋራ ትርክት መገንባት ለዚህ ምክክር ስኬታማነት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፤ ዜጎች በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው የወደፊት እጣ ፈንታቸውን በጋራ እንዲወስኑ ስለሚያግዝ።

በአጠቃላይ የጋራ ትርክት ግንባታ የኢትዮጵያን ያለፈ ታሪክ መካድ ሳይሆን፣ ታሪክን በሚዛናዊነት አይቶ ለተሻለ ነገን የመፍጠር ጥበብ ነው።

ኢትዮጵያ ጠንካራ፣ ዲሞክራሲያዊና የተከበረች ሀገር ሆና እንድትቀጥል የጋራ ትርክት ግንባታ የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው።

ልዩነቶቻችንን ጠብቀን በጋራ የምንኖርባትን ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁላችንም በአዎንታዊ ትረካ ላይ ማተኮር ይኖርብናል።