አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ23ኛው የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ሩብ ፍጻሜውን ለመቀላቀል የሚከናወነው መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት በሁለት ጨዋታዎች ጅማሮውን ያደርጋል፡፡
በዚህም መሰረት አዘጋጇ ሀገር ካናዳ ከሰሜን አፍሪካዊቷና የወቅቱ የአህጉሪቱ ኩራት ሞሮኮ ጋር ምሽት 2 ሰዓት ሂውስተን ላይ ጨዋታዋን ታደርጋለች፡፡
ካናዳ በ32ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ደቡብ አፍሪካን በማሸነፍ እንዲሁም ሞሮኮ ትልቋን ሀገር ኔዘርላንድስን በማሸነፍ 16ቱን የተቀላቀሉ ሲሆን ÷ ዛሬ ምሽትም ለሩብ ፍጻሜው ይፋለማሉ፡፡
በ2022 የኳታር ዓለም ዋንጫ እስከ ግማሽ ፍጻሜ በመድረስ ታሪክ መስራት የቻለችው ሞሮኮ በዘንድሮው ዓለም ዋንጫም ስኬታማ ጊዜን ለማሳለፍ በታላቅ ተነሳሽነት ትጫወታለች፡፡
ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ወቅታዊ አቋማቸው ጥሩ የሚባል ሲሆን ÷ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል በ16ቱ ጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ፓራጓይ ከፈረንሳይ የሚያደርጉት ጨዋታ ሌሊት 6 ሰዓት በፊላዴልፊያ ስታዲየም ይደርጋል፡፡
በመድረኩ ለዋንጫው ተጠባቂ የሆነውና በአሰልጣኝ ዲዲየር ዴሻው የሚመራው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን እስካሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች ሦስት እና ከዚያ በላይ ግቦችን በማስቆጠር በዓለም ዋንጫ ታሪክ የመጀመሪያው ቡድን ነው፡፡
ቡድኑ በማጥቃት ሒደት በተለይም በማይክል ኦሊሴ እና ኪሊያን ምባፔ ጥምረት በርካታ ግቦችን እያመረተ ይገኛል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ለዛሬ ምሽቱ የ16ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር የበቁት ፈረንሳይ ስዊድንን እንዲሁም ፓራጓይ ጀርመንን በማሸነፍ ነው፡፡