የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ማስቀረት የቻለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት

By Abiy Getahun

July 05, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በ2018 ዓ.ም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ማስቀረት ተችሏል አሉ የክልሉ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ ሳዳት ነሻ።

በክልሉ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪነት የተለያዩ ቢሮዎች በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ የ2019 ዓ.ም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ተጀምሯል።

አስተባባሪው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሰፋፊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች ተሰርተዋል።

በዚህም በትምህርት፣ በጤና፣ በደም ልገሳ እና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ አበረታች ውጤቶች ተመዝግቧል ነው ያሉት።

በ2018 ዓ.ም በክልሉ በተሰሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ማዳን መቻሉን ጠቁመው፤ ይህም በህብረትና በአንድነት ከሰራን የማናሳካው ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው ሲሉም ገልፀዋል።

ዘንድሮም የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

በዛሬው ዕለት በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ የተጀመረው ስራም የዚህ አካል ስለመሆኑ አመልክተዋል።

በታምራት ደለሊ