አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ጂኦ ፓርክን የዓለም አቀፍ የጂኦ ፓርኮች መረብ አካል ለማድረግ እየተሰራ ነው አሉ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ።
አካባቢው በዓለም አቀፍ የጂኦ ፓርኮች መረብ አካልነት እንዲመዘገብ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረገ ይገኛል።
የዚሁ ጥረት አካል የሆነ ትምህርታዊ ጉብኝት በአካባቢው ተደርጓል።
በጉብኝቱ ወቅት ሚኒስትር ዴኤታው እንደተናገሩት፤ ጉብኝቱ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው ፓርኩ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) እንዲመዘገብ መሟላት ያለባቸው ጉዳዮች መሟላታቸውን ለማረጋገጥ ያለመ ነው።
መሟላት ካለባቸው ውስጥም አስደናቂ የሥነ ምድር ተፈጥሮ፣ የአካባቢው ማህበረሰብ ከሥነ ምድር ተፈጥሮው ጋር የተዛመደ መሆኑን እና ሌሎች ጉዳዮች መገምገማቸውን ጠቁመዋል።
በቅርቡም ከዩኔስኮ የሚመጡ የኢንስፔክሽን ባለሙያዎች ይህንኑ እንደሚመዝኑ አንስተዋል።
ኢንስፔክተሮቹ በሚሰጡት ውጤትና በሌሎች ዶክመንቶች መሰረት ዩኔስኮ የሚመዘግብ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጂኦ ፓርኩ ምዘናውን አልፎ በዩኔስኮ እንደሚመዘገብ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ጂኦ ፓርኩን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ አስፈላጊ ከሆኑ መስፈርቶች መካከል የአካባቢው ማኅበረሰብ ሙሉ ድጋፍና ፈቃድ እንዲሁም የባህል፣ ታሪክና ተፈጥሮ ውሕደት ማረጋገጫ እንደሚገኙበት ጠቅሰው፤ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙ የጥናት መረጃዎች በአግባቡ መደራጀታቸውን ጠቁመዋል።
ከዚህ ባለፈም በጂኦ ፓርኮች የቱሪስቶች መረጃ ሰጪ ማዕከል፣ አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክቶችና ቢልቦርዶችን ጨምሮ አስፈላጊ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ተከናውነው ጂኦ ፓርኩን ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ዝግጅቶች ተጠናቅቀዋል ብለዋል።
በ14 ወረዳ ውስጥ የሚገኘውና 3 ሺህ 152 ኪሎ ሜትር ስኩየር የሚሸፍነው ጂኦ ፓርኩ ከተመዘገበ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የዩኔስኮ ጂኦ ፓርክ ይሆናል።
በፌቨን ቢሻው