የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የአደጋ ምላሽ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

By Melaku Gedif

July 05, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የአደጋ ስጋት ምላሽ አቅምን ለማጠናከር ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ ተስማምተዋል፡፡

የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ብሔራዊ የአደጋ ስጋት አስተዳደር ባለስልጣን ሊቀመንበር አሊ ሰኢድ አል ነያዲ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

ሊቀመንበሩ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በአደጋ ስጋት አስተዳደር፣ በአደጋ ዝግጁነት እና በአደጋ ምላሽ ላይ ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡

የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በአደጋ ምላሽ ዝግጁነት፣ በሰብዓዊ ሎጂስቲክስ ሥርጭት፣ በቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘ ተሞክሮ እንዳላት ተጠቅሷል፡፡

ኢትዮጵያ ከኢሚሬቶች ጋር በዘርፉ ያላትን ትብብር ማጠናከሯም በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ አደጋዎች ለሚፈጠሩ ችግሮች ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት ያሳድጋል፡፡

ውይይቱ የተቋማዊ አጋርነቶችን ማጠናከር፣ የመገናኛ መንገዶችን ማስፋፋት እና በአደጋ ስጋት ቅነሳ እና የመቋቋም አቅም ግንባታ ላይ የትብብር እድሎችን መለየት ላይ ያተኮረ እንደነበር ተመላክቷል፡፡

በዚህም ሁለቱም ወገኖች የእውቀት፣ የቴክኒክ እውቀት እና የዝግጅትና የምላሽ ሥርዓቶችን ለማሻሻል ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎቸን መለዋወጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።

አል ነያዲ÷ ዓለም አቀፍ ትብብር ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት ሥርዓቶችን ለማሳለጥና እና የችግር ምላሽ አቅምን ለማሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ከወዳጃ ሀገራት ጋር በዘርፉ ልምድ መለዋወጥ ጠንካራ፣ ቀልጣፋ እና ዘላቂ የአደጋ አስተዳደር ተቋማትን በመገንባት ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አስተዳደር አቅምን ለማሳደግ የምታደርገውን ጥረት አድንቀው ÷ በሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብር ይበልጥ ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በአደጋ ስጋት አስተዳደር ላይ እያደገ የመጣው ትብብር በኢትዮጵያ እና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መካከል ያለውን ሰፊ አጋርነት የሚያንፀባርቅ ነው ተብሏል፡፡

የሀገራቱ ትብብር ዘላቂ ልማትን እና የተቋማዊ አቅም ግንባታን በሚደግፉ ተግባራት ላይ እንደሚጠናከርም ነው የተገለጸው፡፡

ኢትዮጵያ ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ከፍተኛ ዋጋ የምትሰጥ አጋር ሀገር ስትሆን÷ ግንኙነቱ በጋራ መከባበር፣ በኢኮኖሚ ትብብር እና በክልላዊ መረጋጋትና የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡