የሀገር ውስጥ ዜና

ከወጪ ንግድ 10 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ተገኘ

By Mikias Ayele

July 06, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በ2018 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 10 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ተገኝቷል አለ።

ሚኒስቴሩ ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር በመሆን የ2018 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማን እያካሄደ ይገኛል።

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በመድረኩ እንዳሉት÷ ተቋሙ ካሉት 67 አገልግሎቶች 47ቱን ወደ ዲጂታል አገልግሎት ቀይሯል።

በዚህም ብልሹ አሰራርን በመከላከልና አገልግሎቶችን ፈጣንና ተደራሽ ከማድረግ አንፃር የጎላ አዎንታዊ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል፡፡

በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አማካኝነት የሚጠየቀውን መስፈርት በማሟላት ተቋማዊ ሪፎርም መደረጉን ገልጸው÷ ለሰራተኞች ምቹ ከባቢ መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያን ለማጠናክር የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመው፤ በርካታ ችግሮች የነበሩበት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ 800 ሚሊየን ብር ትርፍ ማግኘቱን እና የራሱን ህንፃ መገንባት መቻሉን አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ 3 ነጥብ 4 ለሚሆኑ ደንበኞች የንግድ ፈቃድ አገልግሎት መሰጠቱን ተናግረዋል።

የገበያ ሁኔታን ለማረጋጋት በዓመቱ በተሰራ ስራ 800 የቅዳሜና እሁድ ገበያ መስፋፋተቸውን ገልጸው፤ የገበያዎቹ አጠቃላይ ቁጥር 2 ሺህ 869 መድረሱን ጠቁመዋል።

31 የገበያ ትስስር ማዕከላትንም መገንባት መቻሉንም ነው የጠቆሙት፡፡

በአጠቃላይ በዓመቱ አገልግሎቶችን ወደ ኦንላይን መቀየር መቻል፣ ለነዳጅ ቀውስ የተሰጠው ምላሽ፣ የገበያ መሰረተ ልማት ማስፋፋትና የገበያ ማረጋጋት የተሰሩ ስራዎች ስኬታማ እንደነበሩ ተነስቷል፡፡

በክልሎች መካከል የአፈፃፀም ልዩነት መስተዋል፣ የነዳጅ ቁጥጥር ላይ የተስተዋሉ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ውስንነትና ህገ ወጥ ንግድን በሚፈለገው መጠን አለመቀነስ ላይ የአፈጻጸም ውስንነት እንደነበረ ተጠቁሟል።

በታምራት ደለሊ