የሀገር ውስጥ ዜና

በድሬዳዋ ከ56 ሺህ በላይ ዜጎችን ከተረጂነት ማላቀቅ ተቻለ

By sosina alemayehu

July 06, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 3ኛ የሥራ ዘመን 5ኛ ዓመት 12ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው።

የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ በ2018 በጀት ዓመት በተከናወኑ ሥራዎች ዘርፈ ብዙ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡

በዓመቱ መሰረታዊ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በቁርጠኝነት መሰራቱን ጠቁመው ÷ በዚህም የሰንበት ገበያዎችን ወደ 51 በማስፋፋት የዋጋ ንረትን ከ28 በመቶ ወደ 13 ነጥብ 4 በመቶ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ከ56 ሺህ በላይ የአስተዳደሩ ነዋሪዎችን ከተረጂነት ማላቀቅ መቻሉን ነው ከንቲባው አጽንኦት የሰጡት፡፡

በከተማ ማደስና ማስዋብ ዘርፍ በ3 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉንና የተገነባው 17 ኪሎ ሜትር ዘመናዊ መንገድ የንግድ እንቅስቃሴን በማሳደግ ለ10 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡

በትግበራ ላይ ከነበሩት የካፒታል ፕሮጀክቶች መካከል 94ቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውንም አመልክተዋል።

የመንግሥት አገልግሎትን በዲጂታል ለማዘመን በተቋቋመው መሶብ ድሬ የአንድ ማዕከል አገልግሎት 99 ነጥብ 8 በመቶ የተገልጋይ እርካታ መመዝገቡን አብራርተዋል፡፡

ምክር ቤቱ በጉባዔው የቀረበውን ሪፖርት ከመገምገም ባለፈ የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን እንደሚያጸድቅ የአስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመልክቷል፡፡