አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዘመናዊው ዓለም የአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ ከሚወሰንባቸው ምክንያቶች መካከል የባሕር በር ባለቤትነት ዋነኛው ነው።
በዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ውስጥ ከሚጓጓዙ እቃዎች አብዛኛው ከመነሻ ወደ መዳረሻቸው ለማቅናት ባሕርን ይጠቀማሉ፡፡ ወደ ባሕር የሚያደርስ በር መኖሩ ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የንግድ መስፋፋት እና የተወዳዳሪነት መጨመር ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡
የባሕር በር ያለው ሀገር ከውጭ ገበያ ጋር በቀጥታ ይገናኛል፤ ምርቶቹን በቀላሉ ወደ ውጭ መላክና የሚያስፈልጉትን ሸቀጦች በዝቅተኛ ወጪ ከውጭ ማስገባት ይችላል። ይህም የንግድ ትስስርን ከማሳደግ ባለፈ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ያሳድጋል፡፡
በውቅያኖስና ባሕር ትራንስፖርት የሚንቀሳቀሱ የጅምላ ሸቀጦችን በቀጥታ በራስ ወደብ ማስተናገድ የሚከፈል የትራንዚት ወጪን በማስቀረት የሀገር ኢኮኖሚን ያጠናክራል።
ለወጪ ንግድም የጉዞ ጊዜን በማሳጠር በተለይም እንደ አትክልትና ፍራፍሬ፣ አበባ እና ሌሎች ቶሎ ለሚበላሹ ምርቶች ጥራታቸው ሳይጓደል ለዓለም ገበያ እንዲደርሱ ያስችላል፡፡
የባሕር በር ሌላው ጠቀሜታ የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ ሲሆን÷ የመጓጓዣ አገልግሎት ቀላል በሆነባቸው ሀገራት ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ የበለጠ ፍላጎት ይኖራቸዋል። ይህም አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር የዜጎችን ብሎም የሀገርን ኑሮ ያሻሽላል፡፡
በአንጻሩ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የወጪና ገቢ ንግዳቸው በጎረቤት ሀገራት ወደቦች ላይ ስለሚመሰረት፤ለወጪም ሆነ ለገቢ ንግዳቸው የመጓጓዣ ወጪን ከፍ ሊያደርግ፣ የንግድ ሒደቱን ሊያዘገይ እና በፖለቲካዊ ሁኔታዎች ምክንያት የወደብ ተጠቃሚነታቸው በባለወደቦቹ ሀገራት ፍላጎት ላይ ጥገኛ ሊሆን ይችላል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ሰፊ ምዕራፍ ከቀይ ባሕር ጋር ተቆራኝታ የኖረች ሀገር ናት፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የኢኮኖሚና የኃይል ሚዛን አስጠባቂ እንደነበረችም የታሪክ ድርሳናት ይዘክራሉ፤ የቅርብ ጊዜ ትዝታም ነው፡፡
በተሳሳተ የፖለቲካ ውሳኔ የባሕር በር ባለቤትነትን ካጣች በኋላ የወጪና የገቢ ንግዷ በጎረቤት ሀገራት ወደቦች ላይ የተመሰረተ ሆኗል፡፡ይህም በየዓመቱ ቢሊየን ዶላሮችን ለወደብ ኪራይ እንድትከፍል አስገድዷታል፡፡
ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ፤ ከዚህም አብዛኛው በወጣትነት የዕድሜ መጠን ላይ የሚገኝ የሰው ሀብት ያላት ሀገር፤ ብዙ ማምረት ብዙ ማቅረብ አቅሙ እያላት፤ ኢኮኖሚዋ የአቅሟን ያክል እንዳይሻገር ወደብ ተነፍጋ ቆይታለች፡፡
የወደብ ባለቤት ሳትሆን እያስመዘገበች ያለችው ኢኮኖሚያዊ እድገት ወደብ ቢኖራት ምን ያክል ይሆን ነበር የሚለው የበርካቶች ቁጭት ሆኖ ከርሟል፡፡
ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የኢትዮጵያውያን የማደግና የመበልጸግ በአጠቃላይ የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡ኢትዮጵያውያን የባሕር በር ባለቤትነትን በሰላማዊ መንገድ፣ በዲፕሎማሲ እና አብሮ በመበልጸግ እሳቤ መጎናጸፍን ይሻሉ፡፡ ይህንን ለማሳካትም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የባሕር በር ጉዳይን የብሔራዊ ጥቅም ዋነኛ ማጠንጠኛ ማዕከል እንዲሆንና ኢትዮጵያዊያን በአንድነት እንዲቆሙ ከማድረግ አንጻር የአንበሳውን ድርሻ ተወጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ 130 ሚሊየን ሕዝብ የያዘችው ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ድርሻ ሊኖራት ግድ ነው፤ማንም ፈለገም አልፈለገም ኢትዮጵያ ተዘግታ አትኖርም ሲሉ ጽኑ አቋማቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ ከመሽኮርመም ወጥታ ያነሳቸው የባሕር ባር ተጠቃሚነት ጥያቄ በተከናወኑ የዲፕሎማሲ ሥራዎች በዓለም አቀፉ ማሕበረሰበ ዘንድ እውቅና እያገኘ ነው፡፡
ባሕር በር ከተፈጥሮ ሃብት በላይ የኢኮኖሚ ስትራቴጂካዊ እሴት ነው፡፡ ንግድን ያበረታታል፣ ኢንቨስትመንትን ያሳልጣል፤ የሥራ ዕድሎችን ያሰፋል፡፡ በአጠቃላይ የሀገር ኢኮኖሚ እንዲንሠራራ ቀጥተኛ ተጽዕኖ አለው።
ለባሕር በር ጥያቄው ምላሽ ለማግኘትም ኢትዮጵያውያን በብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ላይ ያሳዩት የተደመረ ዕይታና ጽኑ አቋም ትልቅ እመርታ ሆኗል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ማንም ፈለገም አልፈለገም ኢትዮጵያ ተዘግታ አትኖርም፡፡
ምክንቱም ጥያቄው ታሪካዊነትን ከመልክዓ ምድራዊነት፣ ሕጋዊነትን ደግሞ ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጋር ያሰናሰለ ጠንካራና ምክንያታዊ መሠረት ያለው በመሆኑ ነው፡፡
በመልካም ፈቃዱ