አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቋርቋሪ ተቋም የሆነው ሂዩማን ራይትስ ዎች ህገ ወጡ ሕወሃት በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እያደረገ መሆኑን አጋለጠ፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች ባወጣው መግለጫ፤ የሕወሃት ቡድን ከባለፈው ሚያዚያ ወር ጀምሮ እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን ሳይቀር በአስገዳጅነት ለወታደራዊ ዓላማ አስገድዶ እያፈሰ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ህገ ወጥ ቡድኑ የአፈሳ ድርጊቱን ከሚያዚያ ወር ጀምሮ እያከናወነ ስለመሆኑም ተገልጿል።
ከአስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ጋር በተያያዘ ስድስት ጉዳዮችን ማረጋገጥ መቻሉን የገለጸው ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ በክልሉ ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው 18 ሰዎች ህገ ወጡ የሕወሃት ቡድን መሰል ድርጊቶች በስፋት እየፈፀመ እንደሚገኝ አረጋግጧል።
የወርቅ ቁፋሮ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን በማገት ለወታደራዊ አላማ አፍኖ መወስዱንም ገልጿል።
በተመሳሳይ ቡድኑ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ ሲቪል ዜጎችን ለወታደራዊ ዓላማ አስገድዶ እየወሰደ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
ህገ ወጡ ሕወሃት ዜጎችን ለአስገዳጅ ወታደራዊ ዓላማ ማዋሉ በክልሉ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ፍርሃት እንዲፈጠር ማድረጉን ሂዩማን ራይትስ ዎች ጠቁሟል።
ህገ ወጥ ቡድኑ ከእኩይ አላማው በአስቸኳይ እንዲታቀብ ያሳሰበው ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ ለወታደራዊ ዓላማ በተለያየ መንገድ ታፍሰው የተወሰዱ ታዳጊዎች በአፋጣኝ እንዲለቀቁም አስገንዝቧል።
ከአፈሳው በተጨማሪም ከህገ ወጥ ቡድኑ ጥቃት ለማምለጥ የሚሞክሩ ታዳጊዎች ወላጆች ላይ የማሰር እና የማዋከብ ድርጊት እየፈጸመ እንደሆነም ጠቁሟል።