የሀገር ውስጥ ዜና

የሚዲያ ነጻነት ከጋዜጠኝነት ሙያ ሥነ ምግባር ጋር ተጣጥሞ ሊተገበር ይገባል

By Yonas Getnet

July 06, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚዲያ ነጻነት ልቅነት ሳይሆን ከጋዜጠኝነት የሙያ ሥነ ምግባር ጋር ተጣጥሞ የሚተገበር ነው አሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን መምህር መኩሪያ መካሻ ።

መምህር መኩሪያ መካሻ ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷ የሚዲያ ነፃነት እና የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለሚዲያ ኢንዱስትሪው ማደግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው÷ የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ት/ቤቶች ንድፈ ሀሳብን ከተግባር አዋህደው በሙያዊ ክህሎት የታነፀ የሰው ኃይል ሊያፈሩ ይገባል ብለዋል፡፡

ለዚህ ስኬትም የጋዜጠኝነት ት/ቤቶች ተማሪዎቻቸው በንድፈ ሀሳብ የቀሰሙትን እውቀት በተግባር እንዲተረጉሙ የሚያስችሉ የተሟሉ ስቱዲዮዎችን እና ልዩ ልዩ የሥራ ግብዓቶችን ማመቻቸት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ለሀገር ዕድገት የሚዲያ ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት መምህሩ ÷ የልማት ሥራዎችን ለማሕበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ አጀንዳ ቀርጸው ሊሰሩ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ሚዲያው በልማት ሥራዎች ላይ የማይቋረጥ የዘገባ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመው÷ ለሁለንተናዊ ለውጥ ማነቆ የሆኑ ጉድለቶች ሲታዩ ደግሞ በመንግሥት በኩል እንዲታረሙ ማመላከት ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

ስኬቶችን ማሳየት እና የልማት አደናቃፊ ተግባራትን ማጋለጥ አንዱ የሚዲያ ማሕበራዊ ሚና ነው ያሉት መምህሩ÷ ጋዜጠኛው ገንቢ ትችት በማቅረብ የልማት ሥራዎችን ሊያበረታታ ይገባል ብለዋል።

የሚዲያው ቁልፍ እሴት የሀገርን ሉዓላዊነት፣ የሕዝብን አንድነት እና ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ ነው፤ ጋዜጠኛውም ይህንን ማኅበራዊ ኃላፊነት በተገቢው መንገድ መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

እኛ ኢትዮጵያውያን የሚያለያዩን ሳይሆኑ የሚያስማሙን እሴቶች ይበልጣሉ ያሉት መምህር መኩሪያ÷ ሚዲያዎች ይህንን አንድነት የሚያጎሉ አሰባሳቢ ትርክቶች ላይ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በሠራዊት ሸሎ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ከፍል መምህር መኩሪያ መካሻ ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ፡- https://youtube.com/watch?v=HF5C_zxPEZo&si=0Xbx9YSoABGuoKK6