አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ብልጽግና እስኪረጋገጥ ድረስ በጋራ መቆም አለብን አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፤ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ሃሳባችሁን በግልጽ የተናገራችሁ እና በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የሞከራችሁ ሰዎች ጀግኖች ናችሁ ብለዋል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት የምክር ቤት አባላት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበው፤ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የማይናቅ ሚና መጫወታቸውን አመልክተዋል፡፡
ተፎካካሪ ፓርቲዎች በፓርላማ ብቻ ሳይሆን በሌሎች መስኮች ላይም በትብብር እና በጋራ መስራት እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡
የመንግሥት የስራ ኃላፊዎችን፣ ፖለቲከኞችንና የሀይማኖት አባቶችን ተጠቅመን በተቻለ መጠን በእስር ላይ ያሉ ሰዎችን ለመፍታት፣ በውጪ ሀገር ያሉ ሰዎችን በይቅርታ ለማስገባት፣ ጫካ ያሉ ሰዎችን በይቅርታ ለማስገባት ልባችን ሰፊ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
የምንተወው ለኢትዮጵያ ስንል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዕድል እንዳለና አብሮ መስራት እንደሚቻል ማሳየት አለብን ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ሰላማዊና ብልጽግና የተረጋገጠባት ሀገር እንድትሆን በጋራ መስራት እንዲሁም መኖር የምንችል ሰዎች መሆናችንን ዓለም እንዲያይ መተባበርና ልባችንን ማስፋት አለብን ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ከሰላም ውጪ ያለው ጉዳይ ለእኛ አይጠቅመንም በማለት ገልጸው፤ የሚያስፈልገን ብልጽግና እና ልማት ነው ብለዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናችን ሆኖ እንዲያግዘን ጥሪ አቀርባለሁ ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ