የሀገር ውስጥ ዜና

በአዳማ ከተማ በ6 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወጭ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመረቀ

By Mikias Ayele

July 07, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዳማ ከተማ በ6 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወጭ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ክልልና አዳማ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ያስገነባው ፕሮጄክቱ በአዳማ ከተማና አካባቢው የሚኖሩ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ነው የተባለው፡፡

የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ 15 አዳዲስ የከርሰ ምድር ውሃ ምንጮችን በማልማት 5 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መያዝ የሚችሉ 10 ግዙፍ የውሃ ማጠራቀሚያ ቦቴዎችን የያዘ ነው፡፡

በተጨማሪም ፕሮጄክቱ 245 የዋና የሥርጭት መስመሮች፣የውሃ አስተዳደር ቴክኖሎጂ እንዲሁም ባለ አምስት ወለል የአስተዳደር ቢሮ ህንጻ ያለው መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ሰአዳ አብዱረህማን ÷ፕሮጀክቱ በአካባቢው በየጊዜው የሚነሱ የንጹህ መጠጥ ውሃ ጥያቄዎችነን በዘላቂነት  ለመፍታት ያስችላል ብለዋል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ በበኩላቸው ፥ ፕሮጀክቱ መንግስት ዘመናዊ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጄክቶችን ተደራሽ ለማድረግ የሚያድርገው ጥረት አካል መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በቀጣይም በሁሉም የሀገሪቱ ከተሞች መሰል ግዙፍ  የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓቶችን የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ሚሊየን በቀለ (ዶ/ር) ፥ ዘፕሮጄክቱ ዘመኑን በዋጁ መሳሪዎችን የተገነባው እና ንፀሁ ውሃን ሳይቆራረጥ ያለብክነትና ብክለት ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በጎህ ንጉሱ