የሀገር ውስጥ ዜና

የአምስት ዓመት ጉዞ እና የተገቡ ቃሎች አፈጻጸም

By Hailemaryam Tegegn

July 07, 2026

የብልፅግና ፓርቲ በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከፍተኛ ድምጽ አግኝቶ በይፋ መንግሥት ከመሠረተ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል።

ፓርቲው በምርጫ ማሸነፉን ተከትሎ የመደመር መንግሥት ሥልጣን ሲይዝ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በርካታ ቃሎችንና መርሃ ግብሮችን ይፋ አድርጎ ነበር።

የአምስት ዓመት የዕቅድ እና የተግባር ሚዛን፣ የሥልጣን ጉዞ እና የተገቡ ቃሎች አፈጻጸም በአጭሩ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

1. የፖለቲካ ማሻሻያ፣ ሰላም እና ሀገራዊ መግባባት:-

የተገባ ቃል፦ በፖለቲካ ልሂቃን እና በሕዝቡ መካከል የነበሩ የታሪክ ቅሬታዎችን በውይይት መፍታት፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን እንደ ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶች፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያሉትን ከፓርቲ ጣልቃ ገብነት ነፃ ማድረግ እና የሕግ የበላይነትን ማስከበር።

አፈጻጸም፦#ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ፦ መንግሥት በገባው ቃል መሠረት የፖለቲካ ስብራቶችን ለመጠገንና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን በአዋጅ አቋቁሞ ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡ ኮሚሽኑ በየክልሎቹና በየደረጃው ከ200 ሺህ በላይ ከሚሆኑ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አጀንዳዎችን ሲያሰባስብ የቆየ ሲሆን፣ ወደ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለመሸጋገር ዝግጅቱን አጠናቋል።

#ተቋማዊ ነፃነት፦ እንደ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያሉ ተቋማት ከመንግሥት አስፈጻሚ አካል ተፅዕኖ ነፃ ሆነው የራሳቸውን ውሳኔዎች እንዲያሳልፉ የተወሰኑ የሕግና የመዋቅር ማሻሻያዎች ተደርገዋል።

2. ማክሮ-ኢኮኖሚ፣ የከተማ ልማት እና ግብርና:-

የተገባ ቃል፦ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ማስፋት፣ የዋጋ ግሽበትን በምርት ዕድገት መቆጣጠር።

አፈጻጸም፦

#የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፦ ይህ ዘርፍ ፓርቲው ካስመዘገባቸው ታላላቅ ስኬቶች መካከል አንዱ ነው። ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ባደረገችው ሰፊ ርብርብ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመሸፈን አልፋ ምርቷን ወደ ውጭ ሀገራት መላክ የጀመረች ሲሆን፣ ይህም የኢኮኖሚ ጥገኝነትን በመቀነስ ረገድ ትልቅ ምዕራፍ ሆኗል።

#የኮሪደር ልማት እና ሜጋ ፕሮጀክቶች፦ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች የተከናወኑት የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ እና የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የከተሞችን መሠረተ ልማት እና የቱሪስት መስህብነት በከፍተኛ ደረጃ አሳድገዋል።

#የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ፦ መንግሥት ሰፊና ታሪካዊ የተባለ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ለገበያ መተውን ጨምሮ ተግባራዊ አድርጓል። ይህ ማሻሻያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትንና የብድር አቅርቦትን አሳድጓል፡፡ የዋጋ ግሽበትን በምርት ዕድገት ለመቆጣጠርም ከፍተኛ ሥራ ተሰርቷል፡፡

3. ማኅበራዊ ልማት፣ የትምህርት ሪፎርም እና አካባቢ ጥበቃ:-

የተገባ ቃል፦ የትምህርት ጥራትን ማሻሻል፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ማዳረስ።

አፈጻጸም፦#የትምህርት ጥራትና የፈተና ሥርዓት፦ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል አዲስ የትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ በቅድመ መደበኛ እና በአንደኛ ትምህርት ቤቶች ሰፊ የመማሪያ ክፍሎች ማስፋፊያ ሥራ ተሰርቷል፡፡ የተማሪ ምገባ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳያቋርጡ አስተዋጽዖው ከፍተኛ ሆኗል፡፡

#የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፦ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተጀመረው ይህ መርሃ ግብር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል፣ የአፈር መሸርሸርን በመከላከልና የደን ሽፋንን በማሳደግ ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር ትልቅ እውቅናን ያስገኘ ስኬታማ አፈጻጸም የታየበት ነው፡፡

4. የውጭ ግንኙነት እና ብሔራዊ ጥቅም:-

የተገባ ቃል፦ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር፣ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማጠናቀቅ እና የባሕር በር ተጠቃሚነትን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ማረጋገጥ።

አፈጻጸም፦#የታላቁ ሕዳሴ ግድብ፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና የውኃ ሙሌቶች በተከታታይ በተሳካ ሁኔታ ተከናውኖ ኃይል ማመንጨት የጀመረ ሲሆን፣ ይህም የፓርቲው ትልቅ ብሔራዊና ታሪካዊ ስኬት ተደርጎ ይቆጠራል።

#የብሪክስ አባልነት፦ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተደራሽነት ለማስፋትና አዳዲስ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አጋሮችን ለማግኘት የብሪክስ አባል መሆን የቻለች ሲሆን፣ ይህም በዲፕሎማሲው ዘርፍ ትልቅ ስኬት ነው፡፡

#የባሕር በር ዲፕሎማሲ፦ በኢትዮጵያ ለ30 ዓመታት የባሕር በር ባለቤትነትንና ቀጥተኛ ተጠቃሚነትን ማንሳት አሳፋሪ ጉዳይ ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡ ነገር ግን ፓርቲው እሳቤውን በመቀየር ጉዳዩን የአደባባይ አጀንዳ ማድረግ ችሏል፡፡ አጀንዳውንም መላው ህዝብ እና የዓለም ሀገራት ጭምር ገዝተውታል፡፡ የባለቤትነት ጥያቄውን ለማረጋገጥም የዲፕሎማሲ ጥረቶች ቀጥለዋል፡፡

በአጠቃላይ ባለፉት አምስት ዓመታት የመደመር መንግሥት በሜጋ ፕሮጀክቶች፣ በኮሪደር ልማት፣ በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ዘርፎች ላይ ከፍተኛና ተጨባጭ አፈጻጸሞችን አስመዝግቧል።

መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት ዘላቂ ሰላምን በሁሉም አካባቢዎች ለማስፈን ተደጋጋሚ ጥሪዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም ጥሪውን ተቀብለው ተሃድሶ ወስደው ማህበረሰባቸውን የተቀላቀሉ በትጥቅ ይንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት በርካቶች ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች በሰጡት ማብራሪያም ለውይይት ፍቃደኛ ለሆኑት የመንግሥት የሰላም በሮች ዛሬም ክፍት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡