አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ የ2019 ዓ.ም የግል መኖሪያ ቤቶች የአከራይ ተከራይ አዲስ የውል እድሳት ምዝገባ ከዛሬ ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ይካሄዳል አለ የከተማዋ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዜጎችን የኑሮ ጫና ለመቀነስና በኪራይ ገበያው ላይ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥና ዘፈቀዳዊ አሰራሮችን በዘላቂነት ለመግታት የሚወሰዱ ርምጃዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በወጣው የቤት ኪራይ ቁጥጥር አዋጅ መሠረት ለ2019 በጀት ዓመት የሚተገበረው ፍትሃዊ የቤት ኪራይ ዓመታዊ ጭማሪ ጣሪያ 11 ነጥብ 5 በመቶ ሆኖ መጽደቁ ይታወቃል፡፡
ይህንን ተከትሎም በከተማዋ የሚገኙ የግል መኖሪያ ቤቶች የአከራይ ተከራይ አዲስ የውል እድሳት ምዝገባ ከዛሬ ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በይፋ መተግበር ይጀምራል።
የዋጋ ማስተካከያ ውሳኔው በከተማዋ ሰፊ ሳይንሳዊ ጥናት ተካሂዶ የነዋሪውን እውነተኛ የመክፈል አቅም ባገናዘበ መልኩ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡
አሰራሩ አከራዮች ወቅቱንና የኢኮኖሚ ሁኔታውን ያገናዘበ ፍትሃዊ ገቢ እንዲያገኙ የሚያረጋግጥ መሆኑ ነው የተጠቆመው፡፡
በተጨማሪም ተከራዮች ከገቢያቸው ጋር የተመጣጠነ ኪራይ በመክፈል ከተደጋጋሚ መፈናቀልና ከሥነ ልቦና ስጋት ድነው የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ ያስችላል።
ውሳኔው በከተማዋ ያለውን የኑሮ ውድነት ጫና በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ ረገድ የጎላ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና መልካም አስተዳደር ፋይዳዎች እንዳሉት መገለጹንም የቢሮው መረጃ ያመላክታል፡፡፡